ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ፅኑ አቋም አላት-ዶክተር ወርቅነህ

83
ኒው ዮርክ መስከረም 15/2011 ኢትዮጵያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ጽኑ አቋም እንዳላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጹ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሽብርተኝነት መከላከል ጽህፈት ቤት ረዳት ጸሀፊ ቭላድሚር ቮሮንኮቭ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። በውይይቱ ወቅት ዶክተር ወርቅነህ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ዓለም-አቀፍ ስጋት የሆነውን ሽብርተኝነት ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት ጽህፈት ቤቱ የሚያደርገውን ድጋፍ ታደንቃለች። የኢትዮጵያ መንግስት ድህነትን መዋጋት ቀዳሚ ትኩረቱ ቢሆንም ጽንፈኝነትና ሽብርተኝነት ለድህነት ትግሉ ተግዳሮት በመሆናቸው በጽኑ የሚከላከላቸው እንደሆነ አመልክተዋል። የሽብርተኝነት መከላከል ጽህፈት ቤት ረዳት ጸሀፊ ቮሮንኮቭ በበኩላቸው በአፍሪካ ቀንድ የመጣው አዲስ የሰላም ሂደት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው በአየር በረራ ደህንነትና በፍትህ ስርዓት ማሻሻያዎች ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለኢትዮጵያ ለመስጠት ዝግጁነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም