የግብርና መካናይዜሽን መስፋፋት ለምርታማነት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ነው

243

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 26/2015 የግብርና መካናይዜሽንን ለማስፋት የተከናወኑ ስራዎች ለዘርፉ ምርታማነት መሻሻል ከፍተኛ ሚና እያበረከቱ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ሶሰት ዓመታት ለስንዴ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ሲሆን፤ በዚህም የስንዴ ምርትን ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በሚቻልበት ሽግግር ላይ ትገኛለች፡፡

ለዚህ ደግሞ በበጋ መስኖ ብቻ በአገር አቀፍ ደረጃ 52 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማግኘት እቅድ ተይዞ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን፤ እቅዱን እውን ለማድረግ ዘመናዊ የግብርና ግብዓቶች ስርጭት ቀደም ብሎ መከናወኑ ተገልጿል፡፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት በተከናወኑ ስራዎች የስንዴ ምርታማነት በእጅጉ እየተሻሻለ መሆኑን ነው ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ የሚጠቁመው፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ባለፉት ሶስት ዓመታት የመኸር ስንዴ ልማትን በእጥፍ መጨመር መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ከሶስት ዓመት በፊት በክልሉ በመኸር ወቅት በስንዴ የሚለማው መሬት ከ800 ሺህ ሄክታር እንደማይበልጥ ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ቁጥሩ ወደ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር ማደጉን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት በአንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለማከናወን እቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰዋል፡፡

ለምርትና ምርታማነት መጨመር ደግሞ የግብርና መካናይዜሽን ለማስፋት የተከናወኑ ስራዎች ትልቅ ፋይዳ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም አርሶ አደሮች ትራክተርን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ማሽነሪዎችን በብድር እንኳ ማግኘት የማይችሉበት አሰራር እንደነበር ጠቅሰው፤አሁን ላይ ችግሩ መቀረፉን ጠቅሰዋል፡፡

አርሶ አደሩ የግብርና ማሽነሪዎችን በብድር ከቀረጥ ነጻ እንዲያገኝ መንግስት ከፍተኛ ስራ ማከናወኑን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት ወደ አዲስ ምእራፍ እያሸጋገረው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ውጤት አመራሩ ትኩረት ሰጥቶና ህብረተሰብን አስተባብሮ መስራት ከቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን መለወጥ እንደሚቻል አመላካች ነው ብለዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የገጠሟትን አስቸጋሪ ፈተናዎች ተቋቁማ ሰፋፊ የልማት ስራዎችን እያከናወነች መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለው የኢኮኖሚ አቅጣጫ ትክክለኛ መሆኑን ያመላከተ ነው ያሉት፡፡

በቀጣይም ኢትዮጵያን የሚለውጡ በርካታ የልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ በመጥቀስ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም