ኢትዮጵያ ለስንዴ ልማት የሰጠችው ትኩረት ከአገር ውስጥ ባለፈ የዓለም ገበያ የስንዴ ምርት እጥረትን ይቀርፋል

158

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 26/2015 ኢትዮጵያ ለስንዴ ልማት የሰጠችው ትኩረት ከአገር ውስጥ ባለፈ በዓለም ገበያ ያለውን የስንዴ ምርት እጥረት ለመቅረፍ እገዛ እንደሚያደርግ በኢትዮጵያ የፈረንሳይና የብርታኒያ አምባሳደሮች ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር በምእራብ አርሲ ዞን ገደብ አሳሳ እየተካሄደ ያለውን የስንዴ ምርት አሰባሰብ ሂደት ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ከተሳተፉት መካከል በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ፣ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር አልስቴር ማክፔል፣ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን ኦዎር እንዲሁም በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አውጉስቲኖ ፓሌስ እና ሌሎች የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ይገኙበታል፡፡

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ኢትዮጵያ ለስንዴ ልማት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኗን በጉብኝታቸው መመልከታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዓለም የጂኦ ፖለቲካ መለዋወጥ ምክንያት ሰንዴን ጨምሮ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ እጅግ እየናረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ይህም ለዓለማችን ወቅታዊ ፈተና ሆኗል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ለስንዴ ምርት ትኩረት ሰጥታ መስራቷ የሚደገፍ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የፈረንሳይ ኩባንያዎች በተለይ በኢትዮጵያ በቢራ ገብስ ምርት ላይ መዋለ ንዋያቸውን በግብርናው ዘርፍ እያዋሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የብሪታኒያ አምባሳደር አልስቴር ማክፔል በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የስንዴ ምርት እጥረት መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

ለዚህም እንደ ኢትዮጵያ ሌሎች ሀገራት በራስ አቅም ስንዴን በማምረት ለወጪ ንግድ ለማቅረብ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ብሪታኒያ ከኢትዮጵያ ጋር በግብርናው መስክ የተሻለ ትብብር እንዳላት ጠቅሰው፤ በቀጣይ ይህ ትብብር ሊጠናከር ይገባል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ አኳያ በርካታ የብሪታኒያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ሊሰማሩ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በግብርና መካናይዜሽን ወጤታማ ስራ እያከናወነች መሆኗን ተናግረዋል፡፡

የግብርና መካናይዜሽን በተለይ በምርት ወቅት የሚከሰትን የምርት ብክነት በመከላከል ምርታማነትን እንዲጨምር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት ወደተሻለ ደረጃ እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከመኸር በተጨማሪ ለበጋ ስንዴ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ሲሆን፤ በዘንድሮው የበጋ ወቅትም በአገር አቀፍ ደረጃ በ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም ስንዴ በማልማት 52 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እቅድ ተይዟል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴ ለውጭ ገበያ የምታቀርብ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም