በዚህ የመኽር ወቅት ከ400 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል

141

ደሴ፣ ጥቅምት 26 ቀን 2015 (ኢዜአ) በዚህ የመኽር ወቅት በተለያየ ሰብል ከተሸፈነው ከ13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ከ400 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሩብ ዓመት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለሰ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የግብርና ዘርፉን በዘላቂነት ማሳደግ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ የመተካት ና ወደ ውጭ ለመላክ ያስችላል።

ለስንዴ ግዢ ከ700 ሚሊዮን እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይደረግ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህንን ሁኔታ መቀየር የሚያስችል ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

የግብርና ዘርፉን ለማዘመን የማዳበሪያና ምርጥ ዘር አጠቃቀም አንዲሁም በኩታ ገጠምና በመስመር በመዝራት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።

በመሆኑም በዚህ የመኽር ወቅት ብቻ በተለያየ ሰብል ከተሸፈነው ከ13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከ400 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰበ ጠቁመዋል።

ከዚህ ውስጥም 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታሩ በስንዴ ሰብል መሸፈኑንና 108 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተው፤ ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ ለፍጆታ ከሚያስፈልገው 97 ሚሊዮን ኩንታል የበለጠ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።

ከመኽር ምርት በተጨማሪም በበጋ ወቅት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በመስኖ በማልማት 52 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ጥረት እየተደረገ ሲሆን ከሃገር ውስጥ ፍጆታ ውጭ የሆነው የስንዴ ምርትም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጭ ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በመሆኑም በግብርና ዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት በምግብ እራስን ከመቻል አልፎ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን እህል ስኬታማ ለማድረግ የህልውና ጉዳይ ሆኖ እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር አልማዝ ጊዜው በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የግብርና ዘርፉ ፈጣን ለውጥ እንዲያመጣ የሚያስችሉ ስራዎች በቴክኖሎጂ ጭምር በመታገዝ እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።

ክልሉ በሃገር አቀፍ ደረጃ ከሚመረተው የሰብል ምርት 33 በመቶ እንደሚሸፍን ጠቅሰው፤ ከዚህ በላይ ኢኮኖሚውን ማገዝና መደገፍ ይገባል ብለዋል።  

በዚህ የመኽር ወቅት 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በተለያዩ የሰብል ዘሮች መሸፈኑንና ከዚህም ከ143 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

በክልሉ በመኽር በስንዴ ከለማው 832 ሺህ ሄክታር እየተሰበሰበ ካለውና በበጋው ወቅት በመስኖ ከሚለማው 250 ሺህ ሄክታር ከሚሰበሰበው ምርት በአጠቃላይ 7 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ወደ ውጭ በመላክ በሃገር አቀፍ ደረጃ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

የሰብል ልማት እንቅስቃሴውን በቴክኖሎጂ ለማገዝም 500 ኮምባይነር፣ 5 ሺህ አነስተኛ የመውቂያ ማሽኖችን ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በክልሉ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በመስኖ የሚለማ መሬት ቢኖርም እየለማ ያለው ከ240 ሺህ ሄክታር እንደማይበልጥ ጠቅሰው፤ ይህን ለማሻሻል ሰፊ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከሰብል ልማት በተጨማሪም በእንስሳት፣ በአትክልትና ፍራፍሬና ሌሎች ዘርፎች መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣትም የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ ተይዞ እየተተገበረ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም