የምርምርና ጥናት ወጤቶች ወደ ተጠቃሚ ወርደው ተግባር ላይ እንዲውሉ እየተሰራ ነው---ዲላ ዩኒቨርሲቲ

77
ዲላ ግንቦት 11/2010 የጥናትና ምርምር ውጤቶች ከመማር ማስተማር ግብአትነት ባለፈ ወደ ተጠቃሚው ወርደው ተግባር ላይ እንዲውሉ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ዲላ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ ፡፡ ዩኒቨርሲቲው "ጥናትና ምርምር ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ ስምንተኛውን ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤውን ከትላንት ጀምሮ እያካሄደ ነው። በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ስርፀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር አሰበ ረጋሳ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ለህብረተሰቡና ለባለድርሻ አካላት ጋር በሚያዘጋጃቸው የምርምር ጉባኤዎችና በዓመታዊ የህትመት መፅሄት አማካኝነት ስራዎቹ  ለተጠቃሚና ለፖሊሲ አውጪ ተቋማት እንዲደርሱ እያደረገ ነው ። በአምናው ጉባኤ የቀረቡ የጥናትና ምርምር ውጤቶች "አካባቢና ልማት" በሚል ርዕስ በተያዘው ዓመት በመፅሄት መልክ ታትመው ለተጠቃሚ እንዲደርሱ መደረጉን ጠቅሰዋል ። "ስራዎቹ በህትመት መልክ በመሰራጨታቸው የሚመለከታቸውን አካላት በቀላሉ ተደራሽ ማድረግና የመፍትሔ እርምጃ እንዲወስዱ አቅጣጫ ማመላከት ተችሏል" ብለዋል ። የዩኒቨርሲቲው ምሁራን የሕብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናትና ምርምሮችን እንዲያካሂዱ በማበረታታት ከመነሻ ዕቅድ ጀምሮ በምርምር የተገኘው ውጤት ወደ ማህበረሰቡ ወርደው ተግባራዊ እስኪሆኑ ድረስ ክትትልና የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል ። በበጀት ዓመቱ ለምርምርና ስርፀት ማካሄጃ ድጋፍ የሚሆን ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን ጠቅሰዋል ። በኢትዮጵያ የአለም አቀፍ እንስሳት ምርምር ተቋም ተመራማሪ  ዶክተር አዛገ ተገኝ በበኩላቸው የምርምር ጉባኤዎች ሀገሪቱ በሳይንስና ምርምር ውጤቶች የሚመራ ዘላቂ እድገት እንድታስመዘግብ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል ፡፡ "የምርምር ተቋሙ ባለፉት 14 ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት በዝርያ ማሻሻል፣ በመኖና በእንስሳት ሀብት አጠቃቀም 2 ሚሊዮን ለሚሆኑ አነስተኛ ገቢ ላላቸው  አርሶና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ አድረጓል " ብለዋል ። ይሁን እንጂ በሀገር ደረጃ በዘርፉ እየታየ  ያለው ለውጥ አጥጋቢ እንዳልሆነ ጠቁመዋል ። "የችግሩ ዋንኛ ምክንያት በምርምር ተቋማት በተለይ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለው ዕውቀትና የምርምር ውጤት በተግባር እየተደገፈ አለመሆኑ ነው" ብለዋል ፡፡ ዶክተር አዛገ እንዳሉት ለዘርፉ እደገት የሚመለከታቸው አካለላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል። በወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ታደለ ቃበታ በሰጡት አስተያየት "ምሁራን የሚያካሂዷቸው ምርምርና ጥናቶች ወደ ማህበረሰቡ ወርደው ሲተገበሩ አይስተዋልም" ብለዋል ፡፡ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የሚከሄዱ ጥናቶች የሕብረተሰቡን ችግር ለመፍታት ጥቅም ላይ ካልዋሉ የሚያስከተሉት የሀብት ብክነት ቀላል አለመሆኑን ጠቁመዋል ። "ጥናቶች ችግር ፈቺና ተግባር ላይ የሚውሉ ሊሆኑ ይገባል" ያሉት ዶክተር ታደለ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማት  የምርምርና ጥናት ስራዎችን አፈጸፀም በትኩረት ሊከታተሉ እንደሚገባ አመልክተዋል ፡፡ የምርምርና ጉባኤዎች ለፖሊሲ አውጪዎችና አስፈፃሚ አካላት ትልቅ የእውቀት ግብአት እንደሆኑ የገለጹት ደግሞ በአካባቢ ደን ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የፖሊሲ ፕላንና በጀት ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ዳውድ ሙሜ ናቸው፡፡ "ከዚሀ በፊት የሚካሄዱ ጥናቶች የመደርደሪያ ሲሳይ ሆነው የሚቀሩበት ልምድ ነበር" ያሉት አቶ ዳውድ አሁን ላይ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ችግር ፈቺና የፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ምርምሮችን ማካሄድ አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይ ኢትዮጵያ ለምታራምደው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ከዘርፉ ጋር የተያያዙ ጥናትና ምርምሮች ጉልህ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል ፡፡ "ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዩኒቨርሲቲዎችና ምርምር ተቋማት ጋር በመተባበር ለተግባራዊነቱ እየሠራ ነው " ብለዋል ። ለሶስት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ ከፌደራል፣ ከክልል፣ ከዞንና ወረዳ የመጡ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በዩኒቨርሲቲውና በተጋባዥ ምሁራን የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው መሆኑ ታውቋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም