የሠላም ስምምነቱ ለመላው አፍሪካ ያለው ተምሳሌታዊ ፋይዳ የጎላ ነው - ምሁራን

173

ሐዋሳ ጥቅምት 26 ቀን 2015 (ኢዜአ) በመንግስትና ህወሓት መካከል የተደረሰው የሠላም ስምምነት ኢትዮጵያ ካላት ስምና ዝና አንጻር ለመላው የአፍሪካ ሀገራት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የጎላ ተምሳሌታዊ ፍይዳ ያለው መሆኑን ምሁራን ተናገሩ።

መንግስትና ህወሃት የሰላም ስምምነት ማድረጋቸውን ተከትሎ ኢዜአ በሐዋሳ ከተማ ከሚኖሩት የዓለም ታሪክ ምሁር አባቡ አሊጋዝ እና የህግ ባለሙያው አቶ ግርማ ዕርገጠው ጋር ቆይታ አድርጓል።

ምሁራኑ በሰጡት አስተያየት አለመግባባትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚቻል ያሳየ ስምምነት መደረጉን ተናግረዋል።

በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በማስተማርና ጥልቅ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት የዓለም ታሪክ ምሁሩ አባቡ አሊጋዝ እንዳሉት፤ ስምምነቱ የአፍሪካ ሀገራት ችግሮቻቸውን ለመፍታት የአፍሪካ ህብረት ላይ ዕምነት እንዲጥሉም የሚያደርግ ውጤታማ ሥራ ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ግጭት ለሠላም ቅድሚያ በመስጠት መቋጨቱ ትልቅ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ድል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአሁን ወቅት በርካታ የአፍሪካ አገራት ላይ አለመረጋጋትና ግጭቶች መኖራቸውን ያስታወሱት መምህር አባቡ ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ ለመዳኘትና ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ፈር ቀዳጅ የሆነ ስምምነት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱ በቀዳሚነት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እፎይታን የሚፈጥር ነው ያሉት መምህር አባቡ፤ ኢትዮጵያ ካላት የላቀ ስምና ዝና አንጻር  ለመላው የአፍሪካ አህጉር ያለው ተምሳሌታዊ ፋይዳ እጅግ የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ የማበጀት የረጅም ጊዜ ትግል ፍሬው የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

ስምምነቱ የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉአላዊነትን በማስከበር በአሸናፊነት የተቋጨ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጦርነቱ በሠላማዊ መንገድ መፈታቱ ትልቅ ድል ነው ብለዋል፡፡

የህግ ባለሙያው አቶ ግርማ ዕርገጠው በበኩላቸው ስምምነቱ በአንዲት ሀገር ላይ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሕጋዊ መንገድን ብቻ መከተል ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ ማሳየቱን ተናግረዋል።

የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ፣ በህግ መመራትና የህዝብና ሀገር ደህንነት ማስቀደም እንደሚገባ ገልጸዋል።

ስምምነቱ ለህግ የበላይነት ትርጉም አቅም የሰጠ መሆኑን ያነሱት አቶ ግርማ፤ በዚህም የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ፍላጎት የተሳካ መሆኑን ጠቅሰዋል ፡፡

ጦርነቱ በመላው ኢትዮጵያዊያን ላይ ሰብዐዊ፣ ቁሳዊና ኢኮኖሚየዊ ጉዳት አስከትሏል ያሉት አቶ ግርማ የተደረሰው ስምምነት ግቡን እንዲመታና ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም