ኢኒስቲትዩቱ የዋግ በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ አዳዲስ የስንዴ ዝርያዎችን እያላመደ መሆኑን ገለጸ

344

ጎንደር ( ኢዜአ) ጥቅምት 26/2015 የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የዋግ በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ አዳዲስ የስንዴ ዝርያዎችን በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የማላመድና የማስተዋወቅ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።

በኢንስቲዩቱ የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ወረዳ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የሚያላምደውን የዋግ በሽታን የሚቋቋም አዲስ የስንዴ ዝርያ ለተለያዩ አካላት አስጎብኝቷል፡፡

በዚሁ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሊቃውንት ይሄይስ እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለቀቁ የዋግ በሽታን የሚቋቋሙ አዳዲስ የስንዴ ዝርያዎችን የማላመድ ስራ በስፋት እየተሰራ ነው።

ለዚህም በክልሉ የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከልን የስንዴ የልህቀት ማዕከል በማድረግ የዝርያ መረጣና ማሻሻል እንዲሁም የማላመድና የማስተዋወቅ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ለክልሉ ስነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ 'አሊዴሮ'፣ 'ቀቀባ'ና 'አጎልጃ' የተባሉ የስንዴ ዝርያዎችን በምርምር ጣቢያዎች በማላመድ በመኸርና በመስኖ ስንዴ ልማቱን እያገዙ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም 'አሊዴሮ' የተባለው የስንዴ ዝርያ የዋግ በሽታን በመቋቋም በሄክታር እስከ 65 ኩንታል ምርት መስጠት እንደሚችል በምርምር መረጋገጡ በአርሶ አደሮች ዘንድ ተመራጭ አድርጎታል ብለዋል።

በአገር አቀፍ የተጀመረውን የስንዴ ልማት ለማገዝም በዚህ ዓመት በ2 ሺህ 500 ሄክታር ማሳ ላይ የተሻሻሉ ዝርያዎችን የማላመድና በ500 ሄክታር ማሳ ላይ ደግሞ የመነሻ ዘር ብዜት እንደሚከናወን አስረድተዋል።

የዋግ በሽታን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችሉ የስንዴ ዝርያዎችን በዘንድሮ የበጋ መስኖ 1ሺህ ሄክታር ላይ የዘር ብዜትና የማስፋት ስራ ይከናወናል ያሉት ደግሞ የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ሃላፊ አቶ ምንተስኖት ወርቁ ናቸው፡፡

ምርምር ማዕከሉ በሰሜን በምዕራብና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች አካባቢ ለስነ-ምህዳሩ ተስማሚ የሆኑ የስንዴ ዝርያዎችን የማላመድና የማስፋት ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ማዕከሉ በሰሜን ጎንደር ዞን ደብር ቀበሌ በኩታገጠም እርሻ በ30 ሄክታር መሬት ላይ 67 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 'አሊዴሮ' የተባለውን የስንዴ ዝርያ በማባዛትና በዝርያ ማስፋት ላይ አተኩሮ እየሰራ ይገኛል።

"ለረጅም ዓመታት ያለማናቸው ነባር የስንዴ ዝርያዎች የዋግ በሽታ መቋቋም ባለመቻላቸው ከምርት ስራ ውጪ እያደረጉን ነው" ያሉት በዞኑ የደብር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ሰለሞን ተስፋዬ ናቸው፡፡

በ2014/15 ምርት ዘመን በግብርና ምርምር ቀርቦልን በኩታ ገጠም እርሻ ያለማነው የስንዴ ዝርያ የዋግ በሽታን መቋቋም በመቻሉ ምርታቸውን በእጥፍ በማሳደግ 40 ኩንታል በሄክታር እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡

በመስክ ጉብኝቱ ላይ ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ ሞዴል አርሶ አደሮች የግብርና ባለሙያዎች ተመራማሪዎችና አመራሮች መሳተፋቸው ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም