የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ለመጨመር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው- ቋሚ ኮሚቴው

163

ኢዜአ ጥቅምት 25 ቀን 2015 የእናቶችና ሕፃናትን ጤና ለማሻሻልና የሕክምና አገልግሎቱን ተደራሽነትና ጥራት ለመጨመር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

የጤና ባለሙያዎችና አመራሩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያደርሰውን ጉዳት በመቀነስና የመከላከያ ሰራዊትን በሙያቸው በማገዝ ያደረጉት ድጋፍ በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑንም ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።

ቋሚ ኮሚቴው የጤና ሚኒስቴርን የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ሩብ  ዓመት የዕቅድ አፈጻጻም ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ የጤና ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በጠንካራ አመራር የጤናው ዘርፍ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ ያሳዩት ጥረት የሚበረታታ ነው።

የሕክምና አሰጣጡን በማጠናከርና በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም የተሰራው ሥራ በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑንም አመልክተዋል።

ሚኒስቴሩ የአገሪቱን መሪ ዕቅድ መነሻ አድርጎ ጥንካሬና ድክመቶችን በመለየትና የሕዝብን ፍላጎት መሰረት አድርጎ ከወረዳ እስከ ፌዴራል በተናበበ መልኩ እየሰራ ያለውን ስራ ማጠናከር አለበት ሲሉም አክለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡት ግብረ መልሶች ጠቃሚና ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ ነው።

የሕክምና ተደራሽነትና የጥራት ጥያቄ ለመመለስ እንዲሁም በድርቅና በጎርፍ አደጋ የሚከሰቱ ወረርሽኞችን በቅንጅት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው ቋሚ ኮሚቴው ለጤና ሴክተሩ የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የጤና ሚኒስቴርም በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የጤና አገልግሎትን ለማሻሻልና ተደራሽ ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመጥቀስ።

ሚኒስቴሩ ጤናማ ህብረተሰብ ለመገንባት የእናቶች እና ህጻናት ሞት ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም