የሰላም ስምምነቱ አፍሪካውያን ያለማንም ጣልቃገብነት ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚችሉ ያሳየ ነው-የህግ ባለሙያ

113

(ኢዜአ) ጥቅምት 25 ቀን 2015 የሰላም ስምምነቱ አፍሪካውያን ያለማንም ጣልቃገብነት ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚችሉ ያሳየ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው አንድ የህግ ባለሙያ ተናገሩ።

ስምምነቱ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካውያን ተስፋን የፈነጠቀ ነው ብለዋል።

በአፍሪካ ህብረት አመቻችነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በኢፌዴሪ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተካሄደው የሰላም ንግግር ኢትዮጵያውያንን አሸናፊ ባደረገ ስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል።

ስምምነቱ ግጭትን ማቆምና ዘላቂ ሰላም ማምጣት፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ፣ በአንድ ሀገር የአንድ መከላከያ ብቻ መኖርን፣ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ማክበርና ለመገዛት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የህግ አማካሪ እና ጠበቃ ተዋነይ ሙላቱ ስምምነቱ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የተሰጠበት ነው ይላሉ።

በአፍሪካ ህብረት መሪነት የተደረገው የሰላም ንግግር ጣልቃገብነትን እና የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን ተፈጻሚ ማድረግ የሚፈልጉ ኃይሎችን ሴራ ያከሸፈ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰላም ስምምነቱ በብዙ ጥረት የተገኘ መልካም አጋጣሚ መሆኑን በማንሳት ከስምምነቱ ያፈነገጡ ሀሰተኛ መረጃዎችን መጠንቀቅ አለብን ነው ያሉት።

ስምምነቱ በመርህ ደረጃ የተቀመጠ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ የገለጹት የህግ አማካሪው፤ በቀጣይ የሚኖሩ ዝርዝር አፈጻጸሞችን መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በቀጣይም ሰላም ወዳድ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት የሁልጊዜም በጎ ሚናውን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም