በአዲስ አበባ በህገ ወጥ መንገድ የተያዙና ነዋሪ የሌለባቸው 500 ቤቶች ተገኙ

129
አዲስ አበባ መስከርም 15/2011 በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሌለባቸውና በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ 500 ቤቶች መገኘታቸውን የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ። ነዋሪውም በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ ናቸው ብሎ የሚጠረጥራቸውን ቤቶች እንዲጠቁም ቢሮው ጠይቋል። የቢሮው ኃላፊ ኢንጂነር ሰናይት ዳምጤ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስተዳደሩ ከነሃሴ 2010 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በህግ ወጥ መንገድ የተያዙ ቤቶችን ለመለየት መረጃን መሰረት ያደረገ ተግባር  ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህ ማጣራት መሰረትም 500 የሚሆኑ በህገ ወጥ መንገድ የተያዙና  ነዋሪ የሌላቸው መኖሪያ ቤቶች ተሰብስበዋል። እነዚህ የቀበሌና የጋራ መኖሪያ ቤቶች የተሰበሰቡት ከቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ብቻ መሆኑንም ገልጸዋል። በጋራ ቤቶች እጣ ውስጥ በተደጋጋሚ በመግባት የቤት ባለቤት የመሆን፣ ህጋዊ የጋራ መኖሪያ ቤት ፍቃድ ሳይኖራቸው ቤቶችን መያዝ፣ ባለቤት የሌላቸውና የታሸጉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በየክፍለ ከተማውና በቅርጫፍ ጽህፈት ቤቶች በኩል ተሰብስበዋል። በዚህም ''የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል '' ነው ያሉት ኢነጂነር ሰናይት። ኀብረተሰቡ በህገ ወጥ መንገድ የተያዙና ውል የላቸውም ተብሎ የሚገመቱ ቤቶችን በተመለከተም ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር አስተዳደሩ ጠይቋል። ለዚህም በየክፍለ ከተማው ጥቆማ መቀበል የሚያስችሉና የተዳራጁ ቢሮዎች መኖራቸውን የተናገሩት ኢንጂነር ሰናይት፤ ሰነድ ሰብስቦ ጥቆማውን የሚመረምሩ ባለሙያዎችም በየክፍለ ከተማው መመደባቸውን አክለዋል። ይህንን ተግባር ለማቀላጠፍም አስተዳደሩ ነጻ የስልክ መስመር ሥራ ላይ ለማዋል በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸው አስከዚያው ግን በሚከተሉት የስልክ ቁጥሮች ጥቆማ አንዲያደርግ ለህብረተሰቡ ጥሪ አስተላልፈዋል። የካ ክፍለ ከተማ - 0118625950፣ ልደታ ክፍለ ከተማ -0115515500፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ -0118358932፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፣0118697825 ቦሌ ክፍለ ከተማ ፣0118120472፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፣0912151238 በተመሳሳይም ጉለሌ ክፍለ ከተማ ፣0947509969፣ አራዳ 01112677056፣ አቃቂ ቃሊቲ 0911570963፣ አዲስ ከተማ በ0118276627
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም