በዓባይ ወንዝ ላይ የሚነዙ የተዛቡ ትርክቶችን ለማረም በባህል ዲፕሎማሲ ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል

129

(ኢዜአ) ጥቅምት 25 ቀን 2015 ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚነዙ የተዛቡ ትርክቶችን ለማረምና ያላትን ዕውነት ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ የባህል ዲፕሎማሲን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባት ዕውቁ የረቂቅ (ክላሲካል) ሙዚቀኛ ግርማ ይፍራሸዋ ገለፀ።

በ17ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ በተጀመረው ረቂቅ ሙዚቃ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ፣ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩና ግርማ ይፍራሸዋን መሰል ኢትዮጵያውያን ከዘርፉ የሙዚቃ ጠበብት መካከል በጉልህ ይጠቀሳሉ።

ሙዚቀኛው ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ እንደገለጸው፤ ሙዚቃም ሆነ ሌሎች የኪነ-ጥበብ ዘርፎች በየዘመኑ ያጋጠሙ የሕልውና ፈተናዎችን ኢትዮጵያ በድል እንድትወጣ ሚናቸው ጉልህ ነበር።

ኢትዮጵያ አሁናዊ የሕልውና ፈተናዋን ትወጣ ዘንድም ኪነ ጥበብ የአገር አንድነትና ሉዓላዊነቷ እንዲከበር ሚናዋን እየተጫወተች ስለመቀጠሏ ይናገራል።

በቅርቡም ከጥቅምት 30 እስከ ኅዳር 5 ቀን 2015 ዓ.ም ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ ያላትን ዕውነት ለተቀረው ዓለም ለማሳወቅ ግብ የሰነቀ የሙዚቃ ኮንሰርት በአገረ-አውስትራሊያ እንደሚዘጋጅ ገልጿል።

"የዓባይ መንፈስ" የሚል ስያሜ የያዘው ይህ የሙዚቃ ድግስ አርቲስቱን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያ፣ የአውስትራሊያና ሌሎች የዓለም ድንቅ ሙዚቀኞች የሚሳተፉበት ነው።

በአውስትራሊያ ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጋር በመሆን በተሰናዳው በዚህ ኮንሰርት በዓባይ ወንዝ ላይ የሚነዙ ስሁት ትርክቶችን ማረም እና የኢትዮጵያን ሐቅ ለመግለጥ እድሉን እንጠቀማለን ይላል ግርማ ይፍራሸዋ።  

'ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ' እንዲሉ ካለምንም ውጣ ውረድ የሰውን ልጆች እርስ በርስ የሚያስተሳሰር፣ አንድን ማህበረሰብና አገር የሚያስተዋውቅ ጥበብ እንደሆነ ሙዚቀኛው ያወሳል።

በዚህም የኢትዮጵያን ዕውነታ ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ በሙዚቃ መድረኮች ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ሲጠቀም መቆየቱን ይገልጻል።

አገራት ከፖለቲከኞች ባለፈ በባህል መስክ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ተግባራትን እንደሚከውኑ ገልጾ፤ ኢትዮጵያም በባህልና ኪነ ጥበብ ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም በቅጡ ልትጠቀምበት ይገባል ባይ ነው።

ኢትዮጵያ በዓባይ ፖለቲካ መልከ ብዙ ጫናዎች እንደሚደረጉባት በማውሳትም፤ ሙዚቃን ጨምሮ ሁሉንም የኪነ ጥበብ ዘርፎች ተጠቅማ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሐቋን ማሳወቅ እንዳለባት ነው የተናገረው። 

ለዚህ ደግሞ በየክፍልሃተ ዓለሙ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የባህል ዲፕሎማሲን ሁነኛ መሳሪያ አድርገው እንዲሰሩበት ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም