የመገናኛ ብዙሃን ስራዎች የሴቶችና ህፃናትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ያማከሉ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው

123

አዳማ (ኢዜአ) ጥቅምት 25/2015 -- የመገናኛ ብዙሃን ስራዎች የሴቶችና ህፃናትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ያማከሉ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 'የሴቶች ኮከስ' ለምክር ቤቱ ሴት ተመራጮች በህፃናትና ሴቶች ጉዳዮች ዙሪያ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በትብብር መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ውይይት አካሄዷል።

በምክር ቤቱ 'የሴቶች ኮከስ' ሰብሳቢ ወይዘሮ ኪሚያ ጁንዲ እንደገለጹት የመገናኛ ብዙሃን ስራዎች የሴቶችና ህፃናትን ማህበራዊና ኢከኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡና ያማከሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ሴቶችና ህፃናትን በተመለከተ በምክር ቤቱ የሚወጡ ህጎች፣ አዋጆችና ደንቦች ተፈፃሚነት ዙሪያ  መገናኛ ብዙሃን እንዴት ተከታትለው እየሰሩ እንደሆነ ለማየት የሚያግዝ የአቅም ግንባታ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፕሮግራሞች ምን ያህል ሴቶችና ህፃናትን ተጠቃሚ እያደረገ ነው የሚለውን ለማረጋገጥ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

የውይይቱ መድረኩም ማህበራዊ ድረ ገፆችና የህዝብ መገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምና የህግ ማዕቀፎች ዙሪያ ያሉትን ውስንነቶች ጭምር ላይ ያተኮረ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ በበኩላቸው መገናኛ ብዙኃን የሴቶች ተጠቃሚነት ማረጋገጥና በማሳደግ ላይ በትኩረት እንዲሰሩ በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ባለስልጣኑ የስርዓተ ፆታ እኩልነት እንዲረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለሴት የፓርላማ አባላት የተዘጋጀው መድረክ የዚሁ አንድ አካል ነው ብለዋል።

በዚህም የሴቶችና ህፃናት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ በስርዓተ ፆታ ፕሮግራሞች አዘጋገብ፣ ሰፊ ሽፋን ከመስጠት አንፃር፣ የክትትል፣ ድጋፍና ማስታወቂያዎች አሰራር ዙሪያ ለሚዲያ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም