የሰላም ስምምነቱ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማፋጠን ሚናው የጎላ ነው- የኦሮሚያ ክልል የስራ ኃላፊዎች

65

ጥቅምት 25 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሰላም ስምምነቱ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማፋጠን ሚናው የጎላ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል የስራ ኃላፊዎች ተናገሩ፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልል የስራ ኃላፊዎች የውይይቱ በሰላም መጠናቀቅ የሕዝቡ ትኩረት ልማት ላይ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል የመሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጉታ ላቾሬ "ላለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት በርካታ ቀውሶችን አስከትሏል" ይላሉ።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ግጭቱ በዘላቂነት እንዲቆም መስማማቱ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

ስምምነቱ በቀጣይም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ትልቅ እገዛ ያደርግለታል ብለዋል።

በክልሉ የገጠር ልማት ክላስተር የገጠር ዘርፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደስታ ነጌሶ ከምንም በላይ የሰላም ስምምነቱ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማሳካት የሚረዳ ነው ይላሉ።

በስምምነቱ መደሰታቸውን እና ለተፈጻሚነቱም ሁሉም መተባበር እንዳለበት የገለጹት ደግሞ በክልሉ ግብርና ቢሮ የስልጠና ቡድን መሪ ወይዘሮ ሸምሲያ አሊዪ ናቸው።

የሰላም ስምምነቱ እንደ አገር ብዙ ችግሮችን የሚቀርፍና ብዙ ለውጦችን የሚያመጣ በመሆኑ ትክክለኛ እርምጃ መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በችግሮች ውስጥ ሆናም የልማት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በመጨረሱ መልካም ጅምሮች መኖራቸውን ገልጸው የሰላም ስምምነቱን ደግሞ ይበልጥ ፍሬያማ ለማድረግ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም