ለአስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ማህበረሰቡን በነቂስ ያሳተፈ ጠንካራ ሥራ መስራት ይገባል---አቶ ታዬ ደንደአ

132

ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥቅምት 24/2015 በሃገሪቱ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ማህበረሰቡን በነቂስ ያሳተፈ ጠንካራ ሥራ መስራት ይገባል ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ገለጹ።

ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈና በሰላም ዙሪያ የሚመክር መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

ሚኒስትር ዴኤታው በመድረኩ ላይ እንዳሉት የሰላም ጉዳይ ለአንድ አካል ወይም ተቋም ብቻ የሚተው ሳይሆን የመላው ህዝብ የነቃ ተሳትፎን የሚጠይቅ ነው።

በእያንዳንዱ ተቋማት የሚከወኑ ሥራዎች ውጤታማና የታሰበላቸውን ዓላማ እንዲመቱ የህብረተሰብና የተቋማት የተቀናጀ ስራ እንደሚጠይቅም ገልጸዋል።

ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግቦችን ለማሳካት ሰላም የአጀንዳዎች ሁሉ ማጠንጠኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበትና መተባበር ይገባል ብለዋል።

ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የፀጥታ መዋቅሩ ሥራ ብቻ እንዳልሆነ ያመለከቱት አቶ ታዬ፣ የሁሉንም ድጋፍና እገዛ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።

በተለይ ህብረተሰቡን በነቂስ ያሳተፈ ሥራ ቀጣይነት ባለው መልኩ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ይህን ለማጠናከርም ዘላቂ እና ሁለንተናዊ ሰላም ግንባታ፣ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ሁለንተናዊ ሰላም ግንባታ፣በጎ ፈቃድ ለሰላምና ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት የሚሉና መሰል ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች በመንግስት ተቀርፀው እየተተገበሩ መሆናቸውን አቶ ታዬ አስረድተዋል።

"የዛሬው ውይይትም በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ ተቋማት ለሰላም በጋራ እንዲሰሩ ለማስቻልና ተጨማሪ ግብአቶችን ለማግኘት ያለመ ነው" ብለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ በበኩላቸው፣ በክልሉ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም የማስፈኑ ሥራ የፌዴራልንና የራስን የውስጥ አቅም በመጠቀም እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የክልሉ ህዝብ በዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት በዋናነት በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ በተደራጀ አግባብ እንዲሳተፍ እየተደረገ መሆኑንም ነው ዶክተር ሰማ የገለጹት።

"ሰላም የሁሉም መሰረት መሆኑን በመረዳት ህዝብን ያሳተፈ አስተማማኝ ሰላም በአገሪቱ እንዲሰፍን የሰላም ሚኒስቴር እየሰራ ያለው ሥራ የሚደገፍ ነው" ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ከአማራ ክልል ጋር በመተባበር ባዘጋጁት በእዚህ መድረክ የሰላም ሚኒስቴር የሥራ ሃላፊዎች፣  የአማራ ክልል የካቢኔ አባላት እና ሌሎች አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም