በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች በደቡብ አፍሪካ በተደረሰው የሰላም ስምምነት የተሰማቸውን ደስታ ገለጹ

90

ጥቅምት 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) በፈረንሳይ፣ በካናዳ እና ሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን ዋና ጸሀፊ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረሰው የሰላም ስምምነት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሃት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት በትግራይ ክልል የጦር መሳሪያ ድምጽ እንዲያበቃ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የተደረሰው ስምምነት የጠንካራ አመራር እና የሰላም ሂደት ውጤት ነው ብለዋል።

በካናድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው የሰላም ሂደቱ እውን እንዲሆን ለሰላም፣ አንድነትና ሉዓላዊነት በትጋት ለሞገቱ የዳያስፖራ አባላት ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

ውይይቱ በሰላም እንዲደመደም የመከላከያ ሠራዊቱ ለከፈለው መስዋዕትነት ያላቸውን ክብር ገልጸው ዛሬ ሰላምን ይዘን ዋጋ የከፈሉትን ሁሉ በክብር እናስታውሳለን ብለዋል።

በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ "አለም የአመራር ጥበብን ያየችበት ታሪካዊ ክስተት ነው" በማለት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ለኢትዮጵያ ህዝብ ባስተላለፉ የእንኳን ደስ አላችሁ መክዕክት "ከሰላም ሁላችንም ባለድል እንሆናለን" ነው ያሉት።

የተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያውያን የአብሮነት ምሳሌ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል።

ኢጋድ በሰላም ሂደቱ የተጫውተውን ሚና ያነሱ ሲሆን ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም