ደምና ወዙን የሰጠን የኢትዮጵያ አንበሳ ይነሳ ይወሳ!

382

ጀግንነትና ድል አድራጊነት ሲነሳ የኢትዮጵያ አርበኞች ልጅና ያለመሸነፍ ምልክት የሆነው ሠራዊታችን ወይም ወታደር በቅድሚያ ወደ ልባችን ይመጣል ።

ከሠራዊቱ የጀግንነት መገለጫዎች መካከል ክተት ሰራዊት የተባለባቸውን የጦር አውድማ በድል አድራጊነት ተወጥቷል ይህም ከኢትዮጵያ ዳር ድንበሮች አልፎ በተለያዩ ሀገራት ሰላም ማስከበር በተሰማራባቸው ።

ለሠራዊቱ ህልሙም፣ ሀሳቡም፣ ተልዕኮሙም የሀገሩን ሰንደቅ ከፍ ማድረግ፣ ለህዝቡ ደህንነት መረጋገጥ ሁሌም ዋጋ እየከፈለ መሆኑን ታሪክ ይመሰክራል ደሙ የፈሰሰባቸው አጥንቱ የተከሰከሰባቸው ስፍራዎችም ለትውልድ ነጻነትን በመዘከር ህያው ምስክር ሆነዋል።

ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር በአስቸጋሪ በረሃዎችና አጥንት በሚሰብሩ ቀዝቃዛ ስፍራዎችን ተቋቁሞ ሕይወቱን ሳይሰስት በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ተዋድቋል እየተዋደቀም ነው።

ለዚህም ነው ጀግናውን ወታደር የኢትዮጵያ አንበሳ ይወሳ ይነሳ የምንለው። ሞትን በሚያስናፍቁ ስፍራዎች ለሰንደቁ ከፍ ማለት ለሀገሩ ጽናት የከፈለውን ዋጋ በመዘከርና በማመስገን ጭምር።

ይልቁንም ዛሬ ጥቅምት 24ን ስናስብ በተፈጸመበት ክህደት ከጀርባው የተወጋበትን ያስተናገደውን መከራ የምንዘክርበት ዕለት በመሆኑ፤ ጀግናው ወታደር ይወሳ ይነሳ የኢትዮጵያ አንበሳ እያልን የከፈለውን ዋጋ በማወደስ ከጎኑ ቆመን አለኝታነታችንን እንመሰክራለን።

የተካደው ሰሜን እዝ በተሰኘው መጸሃፍ እንደተገለጸው ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም በሠራዊቱ ላይ የተፈጸመው የክሀደትና ጭፍጨፋ ተግባር የውጭ ጠላቶችስ ከዚህ የከፋ ምን ይፈጽማሉ እንድንል የሚያደርግና ባንዳነት የት ድረስ እንደሚጓዝ የሚያሳይ ክስተት ነው።

ከጥቃቱ ቀደም ብሎ የትግራይ ክልልን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ ስፍራዎች የአንበጣ መንጋ ተከስቶ ስለነበር ሰራዊቱ ባለበት ስፍራ ዳር ድንበርን ከማስከበር ጎን ለጎን አንበጣውን ለመከላከል ሲረባረብ ነበር።

ሠራዊቱ ከደሞዙ ቀንሶ የህክምና ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በመገንባት ህዝባዊነቱን አሳይቷል።

ደሙንና ወዙን በሰጠ ጀግና ላይ ነው ታዲያ “መብረቃዊ” በተባለው ጥቃት ዘግናኝ በደል ጥቅምት 24 ቀን 2013 የደረሰበት።

ወታደሩ ወገን አለኝ መከታ አለኝ ሲል በቀበሮ ጉድጓድ ከ20 ዓመታት በላይ ዋጋ በከፈለበት ስፍራም ነው ከጀርባው የተወጋው፤ ጥቃቱ አንኳን በሀገር ሰራዊት ላይ ሊፈጸም ቀርቶ በጠላት ላይ እንኳን ይደረጋል የማይባል ነበር።

ጀግናው ሠራዊት የተቃጣበትን ጥቃት በመመከት የጓዶቹን ደም በአሸናፊነት ተበቅሏል የአባቶቹን ደማቅ ታሪክም በደሙ ጽፏል።

በቀኝ ግዛት ዘመን የነበረውን የባንዳነት ተግባር ያሸነፉ አርበኞች ልጅ የሆነው የኢትዮጵያ ወታደር በዚህ ዘመንም የጀግና ልጅ ጀግና መሆኑን አስመስክሯል።

ያለ ልዩነት ለሀገሩ ክብር ዋጋ የሚከፍለውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት “ጀግናው ወታደር ይወሳ ይነሳ የኢትዮጵያ አንበሳ” እያለን ከጎኑ ቆመን መደገፍ ኢትዮጵያዊ ግዴታችን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም