የዳኝነት ነፃነትንና ገለልተኛነት ማሻሻያ ጥረቶች በግልጽ ችሎቶች ላይ ሊደገም ይገባል

99

ጥቅምት 24/2015 /ኢዜአ/ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዳኝነት ነፃነትንና ገለልተኛነትን ለማሻሻል የተደረጉ ጥረቶች የግልጽ ችሎቶችን በማጠናከር ሊደገም እንደሚገባ አሳስቧል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የ1ኛ ሩብ አመት እቅድና የስራ አፈጻጸምን ገምግሟል።

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች የ2015 የሩብ አመት የእቅድና የስራ አፈጻጸም አቅርበዋል።

ፍርድ ቤቶቹ የዘገዩ መዝገቦችን በተመለከተ ፣የጉዳዮች የፍሰት አስተዳደር፣የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ማጠናከር፣የአንድ መስኮት አገልግሎቶችን ጨምሮ በሁለቱም ፍርድ ቤቶች በሩብ አመቱ የተከናወኑ የእቅድ አፈጻጸም በዝርዝር ቀርበዋል።

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ፉአድ ኪያር፣የዳኝነት አገልግሎትና የአስተዳደር ስራዎችን ተደራሽነትና ተጠያቂነት ለማስፈን በሩብ አመቱ ትኩረት ተሰጥቶት የተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም በመዛግብት አከፋፈት ውሳኔ አሰጣጥ ፣ትዕዛዝ፣ እግድ፣ ብይን ጠንካራ ስራዎች መሰራታቸውን አንሰተዋል።

ፍርድ ቤቶች ዜጎች በነጻነት ያለ አድሎ ሀይማኖትንና ብሄርን መሰረት ያላደረገ አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ግዴታ የተጣለባቸው በመሆኑ ይህን መርህ መሰረት ባደረገ መልኩ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

'' የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ዋጋሪ በበኩላቸው፣ ዳኛ በነጻነት እንዲሰራ በህገ መንግስቱ ነጻነት የተሰጠው ሲሆን ፣ ይህም ተጠናክሮ ሲሰራበት የቆየና ውጤትም ያስመዘገበ እንደሆነ አንስተዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፣ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል እውነቱ አለነ በቀረበው ሪፖርት ላይ በሰጡት ምላሽ፣የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በሩብ አመቱ ከእቅዱ አንጻር ያሳየው አፈጻጸም በመልካም የሚወሰድ እንደሆነ ገልጸዋል።

በሁለቱም ፍርድ ቤቶች ያሉ የሪፎርም ስራዎች አተገባበር በግልጽ የሚቀመጥበት አቅጣጫ በትኩረት ሊታይ የሚገባው መሆኑን አሳስበዋል።

በመሆኑም የፍትህ ስርዓቱ እንዲሻሻል የዳኝነት ነጻነትና ገለልተኛ የሆነ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ኣሳስበዋል።

ፍትሃዊ የሆኑ የዳኝነት ስርዓቱ በተለይ ግልጽ ችሎት ላይ ያለው ችግር አምና የነበረውና የዘንድሮ ተመሳሳይ በመሆኑና የግልጽ ችሎት መኖር ፍትሃዊ የሆነ የዳኝነት ስርዓት የሚረዳ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

የተገልጋይ አርካታ ዝቅተኛ በመሆኑን ጠቅሰው ይህም መሻሻል የሚገባው እንደሆነ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም