የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራትና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ማስፋፋት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል-ቋሚ ኮሚቴ

105

ጥቅምት 23/2015 (ኢዜአ) የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተተኪ አትሌቶችን ማፍራትና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ማስፋፋት ላይ በትኩረት እንዲሰራ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የ2015 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን ዛሬ ገምግሟል።

ሚኒስቴሩ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡ ግልጽ አሰራሮችን በመዘርጋት በአደረጃጀትና በሰው ሀብት አቅም ግንባታ በኩል የጎላ ለውጥ ማምጣት እንደሚጠበቅበት የቋሞ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ አሳስበዋል።

በአትሌቲክስ የስፖርት ዘርፍ ውጤታማ ሥራ መሰራቱን የጠቀሱት ሰብሳቢዋ፤ የተገኘው ውጤት የሚያኮራና የአገሪቱን አንገት ቀና ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ስፍራዎች ለማስፋፋትና ግንባታቸው የተጀመሩትን በፍጥነት ማጠናቀቅ ላይ በትኩረት እንዲሰራም ጠቁመዋል።    

በዓለም አቀፍና አህጉራዊ ውድድሮች ተተኪ፣ ተወዳዳሪና ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራትምም በየክልሉ በስፋት አቅዶ መስራት እንደሚገባም እንዲሁ።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ የአደረጃጀትና የአሰራር ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም