ማህበሩ በደብረ ብርሀን ጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብ ድጋፍ አደረገ

168

ደብረ ብርሃን (ኢዜአ) ጥቅምት 23/ 2015 ክብር ለኢትዮጵያ የልማትና የበጎ አድራጎት ማህበር በሸኔ የሽብር ቡድን ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ።

በአሜሪካን ሀገር ቴክሳስ ግዛት የማህበሩ አስተባባሪ መላዕከምህረት አባ ምህረት ዘውዴ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት፣ ድጋፉ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር በተሰበሰበ ገንዘብ የተደረገ ነው።

"ወገኖቻችን በጊዜያዊ ችግር ምክንያት በመጠለያ ጣቢያ እንዳሉ ተረድተን ካለን ላይ በወገናዊነት ለማካፈል ነው የመጣነው" ሲሉ ገልፀዋል።

ወገኖች አሁን የገጠማቸው ችግር በዘመን ውስጥ የሚከሰት ክስተት መሆኑን በመረዳት ይህን ወቅታዊ ችግር ተጋግዞ ለማለፍ በአብሮነት መረዳዳት እንደሚገባም ገልፀዋል።

የተፈናቀሉ ወገኖችን ችግር ለማቃላል ሁሉም መረባረብ እንዳለበት ጠቅሰው፣ "ማህበሩ የእነዚህ ወገኖች ችግር እስኪፈታ ድረስ ድጋፉን ያጠናክራል" ብለዋል።

የክብር ለኢትዮጵያ የልማትና የበጎ አድራጎት ማህበር መስራች አቶ ሰላሞን አሰፋ በበኩላቸው፣ ከዚህ በፊት የወገኖችን ችግር ለመጋራት ማህበሩ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ዛሬ ተደረገው ድጋፍ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው 400 ኩንታል የዳቦ ዱቄት መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይም አጋር አካላትን በማስተባበር ድጋፉ ተጠናከሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ ከ26 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወገኖች እንዳሉ የገለፁት ደግሞ የደብረ ብሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ናቸው።

እነዚህ ተፈናቃይ ወገኖች ቀጣይነት ያለው ድጋፍ የሚሹ በመሆኑ ሁሉም በሚችለው ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ከምስራቅ ወለጋ ዞን የተፈናቀሉት አቶ መሐመድ አደም በበኩላቸው ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፣ መንግስት የአካባቢውን ሰላም አረጋግቶ ወደቀደመው ቀያቸው እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም