አሸባሪው ህወሃት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት የአገርን ዳር ድንበር ለማስደፈር ያለመ የክህደት ድርጊት ነው - የቀድሞ ሰራዊት አባላት

170

ሶዶ፣ ጥቅምት 23 ቀን 2015 (ኢዜአ) አሸባሪው ሕወሃት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት የአገር ዳር ድንበርን ለማስደፈር ያለመ የክህደት ድርጊት እንደሆነ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ገለጹ።

የወላይታ ዞን የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ማህበር ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ታምራት ሞላ፤ ከምስረታው ጀምሮ ዘራፊና ህገወጥ የሆነው ህወሃት በተንኮልና ሴራ ስልጣን መቆናጠጡን አስታውሰዋል።

ቡድኑ በስልጣን ዘመኑም ሆነ በህዝብ ተቃውሞ ከተሰናበተ በኋላ ኢትዮጵያና ህዝቦቿን በዘር፣ በሐይማኖትና ጎሳ ሲከፋፍልና ሀብቷን ሲመዘብር ቆይቷል ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት ኢትዮጵያን በማዳከም ለታሪካዊ ጠላቶቿ አጋልጦ ለመስጠት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ቡድኑ በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ድርጊት ታሪክ የማይዘነጋው በመሆኑ ሊታሰብ ይገባል ብለዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ አገርን በማዳከም ዳር ድንበሯን ለማስደፈር ያደረገው ሙከራ እንደማይሳካ የአገር መከላከያ ሰራዊትና የኢትዮጵያ ህዝብ ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

"አሸባሪው ህወሃት አገርን ለውጪ ጠላቶች አሳልፎ በመስጠት ክብሯን ለማስደፈር ከፈፀመው የጭካኔ ተግባር ሁሉ የጥቅምት 24 አይረሴው ነው" የሚሉት ደግሞ ሌላኛው የቀድሞ ሰራዊት አባል መቶ አለቃ ታምሩ ቶማ፤ በሰሜን ዕዝ ሠራዊት አባላት ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ጥቃት ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደት እንደሆነ ገልጸዋል።

ቡድኑ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ግንባር ፈጥሮ የአገር ባለውለታ የሆነውን ሰራዊት በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፉ የአገርን ዳር ድንበር ለማስደፈር አልሞ የፈፀመው ነው ብለዋል።

ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማዳከም የፈፀመው ድርጊት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስደፈር የተሞከረበት እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም