ጥቅምት 24 በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ክህደትና ጥቃት የዘመኑ የታሪክ ጠባሳ ነው --- የቀድሞ ሰራዊት አባላት

337

ደሴ፣ ጥቅምት 23 ቀን 2015 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመው ጥቃት ትውልድ ሊማርበት የሚገባ የዘመኑ የታሪክ ጠባሳ ነው ሲሉ የቀድሞ መከላከያ ሰራዊት አባላትና ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ገለፁ፡፡

የቀድሞው መከላከያ ሰራዊት አባል ወታደር አባይ ደርሶ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እድሜውን በሙሉ በህዝብና በአገር ላይ ክህደት ሲፈጽም የኖረው አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመው ክህደትና ጥቃት እጅግ አሰዛኝና አሳፋሪ ነው፡፡

ሰራዊቱ በጀርባው በራሱ ወገን መጠቃቱና መደፈሩ መቼም ሊረሳ የማይችል በደል እንደሆነ ተናግረዋል።

ድርጊቱ በዘመኑ የተፈፀመ ዘግናኝና ሊደገም የማይገባው እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህ የማይረሳ የታሪክ ጠባሳ ትውልዱ ሊማርበት ይገባል ብለዋል።

ለአገሩ ሲል ቤቱን ትቶ በቀበሮ ጉድጓድ ህይወቱን የሚገፋን ታላቅ ሰራዊት ለማዋረድ የተፈጸመው ድርጊት ኢትዮጵያውያን ለአገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አክብሮት የሚጨምር መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ምልክት መተንኮስና ማጠልሸት ከቶውንም አይቻልም፣ አንፈቅድምም ብለዋል፡፡

''ጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ብሔራዊ ኩራታችን፣ የጥቁር ህዝቦች ምሳሌ፣ የሐገር ዋልታና ማገር በመሆኑ የሚከበር፣ የሚወደድና የሚደገፍ ሙያ ነው'' ያሉት ደግሞ ወታደር ሰይድ አሊ ናቸው፡፡

ሰሜን ዕዝ በአሸባሪው ህወሃት የደረሰበት ጥቃት መቼም የማይረሳ ክህደት መሆኑን ተናግረዋል።

በድርጊቱ የተሰዉ የሰራዊት አባላት የሚካሱት የአገርን አንድነትና ሉዓላዊነትን በማስቀጠል እንደሆነ ገልጸው፤ ከሰራዊቱ ጎን ሆነው የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑ አረጋግጠዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ጽህፈት ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ አየለ ወልደ ጊወርጊስ በበኩላቸው ለአገር ኖሮ ለአገር ከሚሞት ሰራዊት ጎን መቆም አገርን መጠበቅ እንደሆነ ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት የሰሜን ዕዝ አባላትን በግፍ መጨፍጨፉ ያደገበትን ሴራ ያጋለጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰራዊቱን ሳይሆን አገርና ህዝብን አዋርዷል፣ ደፍሯል ያሉት አቶ አየለ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሰራዊቱ ጎን ተሰልፎ የሽብር ቡድኑን እንዳይነሳ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ሌላው የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባል ሃምሳ አለቃ ባለምዋል መለሰ በበኩላቸው ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ሃዘንና ብስጭት እስካሁን ከውስጣቸው አለመጥፋቱን ገልጸዋል፡፡

ትውልደ ከዚህ ታሪካዊ ስህተት ተምሮ አንድነቱንና ሰላሙን በመጠበቅ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በጋራ መጠበቅ አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም