"መቼም፣ የትም፣ በምንም አንረሳትም……ያችን እለት!"

197

በእንግዳው ከፍያለው (ባህር ዳር ኢዜአ)

የተረገመች እለት፣ የተረገመች ሌሊት… ከሰይጣን እሳቤም በላይ የሆነች ዘላለም በመጥፎ ስትዘከር፣ ስትነሳ፣ ስትታወስ የምትኖር ሌሊት ናት- ጥቅምት 24 ቀን 2013ዓ.ም። የጨለማ መጋረጃ በእዚህች ምድር ላይ የተዘረጋባት፤ የሰው ልጅ ህይወት በነፍስ ውጭ ግቢ ትንቅንቅ የጣረ ሞት ጩኸት ያስተጋባባት እርጉም እለትም ናት ማለትም ይቻላል ቀኗን። ዕለቷን ስናስብ ስንት ጀብዱ እየፈጸመ የሀገሩን ክብር ያስጠበቀ ጀግና ደሙ በሴረኞች ምክንያት በከንቱ የፈሰሰባት፤ አጥንቱን የከሰከሰባት እና ህይወቱን ጭምር ለመስዋዕት አሳልፎ የሰጠባትን ጥቁር የታሪክ ጠባሳ ከፊታችን ድቅን ይላል። ሁለት ዓመት ወደኋላ ሄደን ቀኑን ስናስብ ፈጣሪ መርገምቱን ያሳረፈበት ነው ማለት ይቻላል።

የዘመናችን ይሁዳዎች አቅምና ጊዜ አገኘን ብለው እንደ ሚዳቋ እየዘለሉ የመከላከያ ሠራዊታችን ያረዱባት፣ የጨፈጨፉባት፣ በጅምላ የረሸኑባት…እለት። የይሁዳ አስተሳሰብ፣ አመለካከትና ድርጊት የተጠናወታቸው እነዚህ የዘመናችን እብሪተኞች በአገራችን የተከሰቱባት እለት እነሆ ሁለት ዓመት ሆነው።

ጥቅምት 24 በአገራችን አስከፊውና ዘግናኙ ታሪክ የተመዘገበባት እለት ሆና በትውልድ ስትታወስ ትኖራለች። ያችን እለት “የተካደው የሰሜን እዝ” በሚለው መጽሃፍ ላይ ደራሲው “ጥቁሯ ቀን” በሚል ገጽ 39 ላይ ገልጿታል። እውን ያችን የሰቆቃና ዋይታ እለት “ጥቁር” የሚለው ቃል ብቻ ይገልጻት ይሆን? ምላሹን ለእርስዎ ልተወውና እንደእኔ እለቷን ከጽልመት የላቀ ገላጭ ቃል ቢገኝ እንኳ ይገልጻታል ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም ድርጊቱ ከአዕምሮ በላይ ነውና።

የአሸባሪው ህወሓት አመራሮችም ለ27 ዓመታት ሀገር በበላይነት እንዲመሩ ያገኙትን እድል ያለአግባብ ለሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ለልማት ኢፍትሃዊነት፣ ለመከራና ስቃይ አዋሉት። ህዝብ በአንድነት አልመጠናችሁም ብሎ ከ4 ኪሎ ቤተ መንግስት ፈንቅሎ ሲጥላቸው መቀሌ በመከተም  ይባስ ብለው ለ20 ዓመታት በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ የትግራይን ህዝብ ሲጠብቅ፤ የትምህርትና የጤና ተቋማትን ሲገነባ፤ የአቅመ ደካሞችን ሰብል ሲዘራ፣ ሲያጭድና ወቅቶ ቤት በማስገባት ሲደግፍ የኖረውን የአብራኩን ልጅ - የሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ፊቱን ለውጭ ጠላት ባዞረበት ወቅት ከጀርባ ያልታሰበ ጥቃት በመፈጸም ለእልቂት ዳረጉት።

ሴራው ቀደም ብሎ የተጠነሰሰ በመሆኑ የሠራዊቱን አመራሮችን በግብዣ ስም በመመረዝና አግቶ በመያዝ፣ የመከላከያ መገናኛ መስመሮችን በመበጣጠስ፣ መሳሪያቸውን በመጋዘን በመቆለፍ፣ የራሳቸው ሰው የሆነውን የሰራዊት አባልና አመራር ቀድመው በዘረጉት ስውር ሴራ ተባባሪያቸው በማድረግ የስንት ሀገር ሰላምን ያስከበረ ጀግና በተኛበት የእልቂት ናዳ አወረዱበት።

የአገራችን ሉዓላዊነት የመጨረሻ ምሽግ፣ መመኪያና አርማ የሆነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በማጥቃት ሀገር የማፍረስ ሴራቸውን አንድ ብለው ጀመሩ። የኢትዮጵያን ህዝብ መከታ፣ መጠጊያና ከለላ ለማሳጣት ከሁለት ዓመታት በላይ የዘለቀውን የእብሪት ዝግጅታቸውን በአደባባይ በግልጽ ያወጁባትን ይሄን እለት ጥቅምት-24ን መቼም... አንረሳትም።

በዓለም ላይ የአንድ ሃገር መከላከያ ሠራዊት በራሱ ወገን ያውም ሲያገለግለው በኖረና ዋጋ በከፈለለት እንደዚህ ጥቃት ደርሶበታል ተብሎ የተጻፈ፣ የተነገረና የታየ ታሪክ የለም። ይሄ የአረመኔነት ጥግ የታየበት ጥቃት የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ...አገራት ሠራዊት ላይ ደርሶ ቢሆን ኖሮ ምን ሊፈጥር እንደሚችሉ ማንም ሊገምት አይችልም።

ለእዚህ ከዓመታት በፊት መስከረም 1 ጥቃት በኒዮርክ ከተማ ሲደርስ አፍጋኒስታን ላይ ያደረሱትን ማስታወስ በቂ ነው። ይህ አኩይ ድርጊት በእዚች የባህልና የሃይማኖት ልእልና ባላት አገር እውን ሆኗል። ከብርሃን የፈጠነ ርምጃ ወስደን የሰሜን እዝን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረነዋል ብሎ የህወሓቱ ሴኮቱሬ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርቦ መስክሯል። በጽንፈኛ ሚዲያቸው እምበር ተጋዳላይ….አስጨፍሯል። ምንም እንኳ ጭፈራውና ደስታው ከደቂቃ ባይዘልም።

የእዚህ ጥቃትም ሆና ከእዚህ በኋላ ህወሓት የለኮሳቸው ጦርነቶች ዓላማና ግቡ ሠራዊቱን በማፍረስ መልሶ ስልጣንን በመቆናጠጥ ሀገር የመሆን ፍላጎት ነው። ለዓመታት ያለከልካይ ባልተገባ መንገድ የያዙት የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነትም ነው። የህወሓት አመራሮች በአዲስ አበባ ከተማና በተለያዩ አካባቢያዎች የገነቧቸው ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን በእጃቸው ማስገባት ካልሆነም ሌላውን የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በእርስ በማጫረስ ታላቋን የህልም ትግራይ መስርቶ በህዝቡ ትክሻ ላይ ስልጣን ተቆናጦ ህዝብን እየጨቆነ ተንደላቆ መኖር ነው። ለዚህ ደግሞ እንደ ሸኔ ያሉ አጫፋሪዎችን በየአካባቢው ከጎናቸው አሰልፈዋል።

የዘመኑ ይሁዳዎች ብልጣብልጥነትና እብሪት የትዬለሌ ነው። የራሳቸውን ልጆች አሜሪካና አውሮፓ አንደላቀው እያስተማሩ የጭቁኑን የትግራይ ክልል ህዝብ ልጆችን ግን በአደንዛዥ እጽ አስክረው ጦርነት በመማገድ ያስጨርሳሉ። ለስልጣን ጥም ፍለጎታቸው ማሳኪያ፣ ለስሜታቸው ማርኪያ፣ ለቀልባቸው መመለሻ... በማድረግ የፈጸሙት ተቆጥሮ የማያልቅ ግፍና በደል ነገ ከነገ ወዲያ ዘግይቶም ቢሆን ለትይግራይ ክልል ህዝብም መገለጹና እውነቱን ማወቁ አይቀርም።

የአገራችን ታሪካዊ ጠላቶችም በህዝብ የተመረጠውንና የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት የሆነውን መንግስት ወደ ጎን በመተው ለሽብር ቡድኑ "አጉራሽ፤ አልባሽ" በመሆን መሰለፋቸው ፍንትው ብሎ በገሀድ የተገለጠው በጀግናው ሠራዊታችን የተመታው ቡድን ነፍስ አውጪኝ ብሎ ደደቢት ዋሻ በገባበት ወቅት ነው። እነዚህ ታሪካዊ ጠላቶች በሰብአዊ ርዳታ ሰበብ የሳተላይት መገናኛ፣ ለሴራ ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ የዘመናችን ይሁዳዎቹ የተገነዙበትን ገመድ በጣጥሰው፣ የተቀበሩበትን አፈር አራግፈው እንዲነሱ አግዘዋል።

ይሄን የአንዳንድ የውጭ ሃይሎች ከእውነት በተቃራኒው የቆሙበትን ክስተት የታሪክ ምሁራን በሳይንሳዊ መንገድ መርምረው የሚያቀርቡት ቢሆንም የታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ጥቅምት 24ን ስንዘክር የይሁዳዎቹም ሆነ የአዛዥ ታዛዣቸው የክፋት ጥግ በመላ ኢትዮጵያውያን ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተወሳ የሚኖር መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም

“ወንድ ልጅ በጥይት ይገደላል እንጂ እንዴት በላዩ ላይ መኪና ይነዳበታል?…ያውም በወገን..!” ሲል ስሜቱን መቆጣጠር አቅቶት እንባውን በአይኖቹ መንታ መንታ ያፈሰሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ልቅሶ እንዴት ይረሳል። ለ20 ዓመታት የትግራይ ክልል ህዝብ ወገኔ ነው ብሎ ሲጠብቀው በኖረውና ስንት ልማት በሰራለት ሠራዊት ላይ ማን በላዩ ላይ መኪና ይነዳበታል ተብሎ ያስባል?። አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ይሄ ከአዕምሮ በላይ የሆነ ሰይጣናዊ ድርጊት ነው።

ሴት ልጅ እናት፣ እህት፣ አገርም ናት። በሴት ልጅ ብል ቢለዋ ...ሌላም ባዕድ ነገር አይላክም… የሴት ልጅ ጡት አይቆረጥም” እነሱ ግን የሽብር ቡድኑ አባላት ይህንን አደረጉት… እያለች እንባዋን በጉንጮቿ እንደ ክረምት ጎርፍ ያወረደችው የመከላከያ ጓዲት እንባስ እንዴትስ ከህሊና ሊወጣ ይችላል? እነዚህና ሌሎች የሠራዊት አባላት ለተፈጸመው እኩይ ድርጊት ሁሉ ህያው ምስክር ናቸው። ከዚህ በላይ ግፍ፣ ከዚህ በላይ ጭካኔ፣ ከዚህ በላይ ሰቆቃ…በዓለም ላይ ታይቶም፤ ተሰምቶም አያውቅም። እንባቸውም የራሄል እንባ ሆኖ ሳይውል ሳያድር የጥፋት ቡድኑ የተወሰኑ አመራሮች በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን ድባቅ ተመተው እንደ አይጥ ከጉድጓድ በቃሬዛ ጭምር ሲወጣ አሳይቶናል።

በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይሄ ግፍና የጭካኔ ተግባር ወደ ጎን ተትቶ የይሁዳዎች ድምጽ ከፍ ብሎ ሲሰማ በዓለም ላይ ፍትህ የት ነው ያለው? ያስብላል። በእኛ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ግን የጀግኖቻችን እንባና የደረሰባቸው በደል ከአዕምሯችን መቼም... ለአፍታም አይጠፋም። ምንም እንኳ አንዳንድ ምዕራባዊያን በሠራዊታችን ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዜ ተመቶ ጉድጓድ ውስጥ የገባውን አሸባሪ ቡድን በሰብአዊ ድጋፍ ሰበብ እንደገና እንዲያንሰራራ ቢያደርጉትም ኢትዮጵያውያን መቼም፣ የትምና በምንም ይሄን የሀገር ጸር የሆነ አሸባሪ ቡድን በመደምሰስ የአገራቸውን ሉአላዊነት ከማስከበር፣ ኢትዮጵያንም ከማጽናት ወደኋላ አይሉም። ምክንያቱም የአድዋ ገድልን የፈጸሙ አባቶቻችን ልጆች ናቸውና።

ቀን አንበጣ ሲያባርር፣ የአቅመ ደካሞችን አዝመራ ሲሰበስብና ሌሎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ስራዎችን በመስራት ሲደክም የዋለውን ሠራዊት ማታ አገር አማን ብሎ በተኛበት ከጀርባ መውጋት የዘመናችን ይሁዳዎች ሰይጣናዊ ድርጊት ጥግ ማሳያ ነው። ከ5 ሺህ ዘመናት በላይ የሀገረ መንግስት ታሪክ ያላትን አገር ጠንካራ ምሽግና መከታ የሆነውን መከላከያ ሠራዊተን በመምታት ሀገር የማፍረስና ህዝብን ለችግር የመዳረግ ህልማቸውን ለማሳካት የፈጸሙት እንደሆነ የዘመናችን ይሁዳ አመራሮች በተለያየ ጊዜ የሰጡት መግለጫ ያሳያል።

ይህች ቀን በየዓመቱ እንድትታወስ መወሰኑ በሥራዊታችን ላይ የደረሰውን ሰቆቃ፣ ግፍና በደል ከመዘከር ባለፈ እንደቅርጫ ልትከፋፈል ጫፍ ደርሳ የነበረችው አገራችንን ለማዳን የተቻለበት የአመራር ጥበብ አብሮ መታወስ ይኖርበታል።የመከላከያ ሠራዊታችን ጀግንነት፣ የመላ ህዝቡ አንድነትና ጽናት እንዲሁም በየምዕራፉ እየጎመራ ያለው አኩሪ ድል ሚስጥሩም እንዲሁ ሊመረመር ይገባል።

ጥቅምት 24 ውድ ሕይወታቸውን አስይዘውና የገጠማቸውን መሰናክል በጣጥሰው ለማለፍ በፈጸሙት ተጋድሎ  ለአገር መከታ፣ ኩራትና አለኝታ የሆኑ የሠራዊት አባላትና አመራሮች የተፈጠሩባት እለት መሆኗም አይዘነጋም። ዕለቱ ሀገር አፍራሽ ይሁዳዎች እጃችንን አንሰጥም በማለት ያለምግብና ያለውሃ እስከ አምስት ቀን ድረስ እየተዋጉ የወገን ጦር የደረሰላቸው፣ በፊታቸው የሚገጥማቸውን ይሁዳ ሁሉ ነፍሱን ወደ ሲኦል፤ ሥጋውን ወደ አፈር እየቀላቀሉ… ኤርትራ የገቡ የሰሜን እዝ ክፍለ ጦሮች፣ ሻለቃዎች… ታሪክ የሚዘከርበት እለት መሆኑ ደረትን ነፍቶና አንገት ቀና አድርጎ ለመራመድ ያስችላል።

አገር ከሚፈርስ እኔ ቀድሜ ልፍረስ ብለው እንደገና የተበተነ ሠራዊታቸውን አደራጅተው፣ ትጥቃቸውን አጠባብቀው፣ ያሏቸውን መሳሪያዎች አቀናጅተው ተመልሰው ወደትግራይ በመግባት አንዱ ወታደር እንደ 15 እና 20 ወታደር ሆኖ በቁጭት የተፋለሙና ድል ያስመዘገቡ ጀግኖች እንዲፈሩ ጥንስስ የተጠነሰሰባት እለት ጭምር ናትና ልትዘከር ይገባል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን አንተ ኦሮሞ ነህ፣ አንተ አማራ ነህ፣ አንተ ደቡብ ነህ….እያሉ በመከፋፈል ከልባቸው በቅሎ፣ አድጎና ጎልምሶ ፍሬ ያፈራውን በቀላቸውን ፈጽመው ያሰዩባት የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ታሪክ ፈጽሞ ተነግሮም ሆነ ተጽፎ የሚያልቅ አይደለም። “ዓባይን በጭልፋ” እንዲሉ በእዚህ ጽሁፍ ጥቂት በደሎችን ለማሳየት ሞከርኩ እንጂ ያልተጻፉና ያልተነገሩ ብዙ የህወሓት የጭካኔ ተግባሮች አሉ።

ችግሩ ከሰሜን እዝ ጥቃት እስከ ደደቢት ዋሻ፣ ከዛም መንግስት የሰጠውን የጽሞና ጊዜ በመጣስ ወደ ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ጎንደርና አፋር ክልል ደርሷል። ከስህተታቸው መቼም የማይማሩት የዘመኑ ይሁዳዎች (የህወሓት አመራሮችና ታጣቂዎቹ) ዳግም በንጹሀን ዜጎች ላይ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ሃብትና ንብረት መዝረፍ ወንጀሎችን ፈጽመዋል። አብሮ የኖረውን የትግራይ ህዝብ ከአማራና አፋር ህዝብ ጋር ለማቃቃር ሌት ከቀን ጣሩ፤ ብዙ ዳገትና ቁልቁለትም ወጡ ወረዱ። ይሄ ጥፋትም አብሮ በትውልድ ሲዘከር ይኖራል። ይህን "በሰሜን እዝ ላይ የተፈፀመውን ክህደት የሚዘክር ሃውልት ሊቆም ይገባል" የሚል የብዙዎችን አስተያየት እኔም በመጋራት ለዛሬ ጽሁፌል ልቋጭ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም