የአለም የጤና ድርጅት በጤናው ዘርፍ ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

107

ጥቅምት 23/2015(ኢዜአ) የአለም የጤና ድርጅት በሀረሪ ክልል በጤናው ዘርፍ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚስያቀጥል በድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ቦሪማ ሳንቦ አስታወቁ ፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ቦሪማ  ሳንቦ የተመራ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች በሀረሪ ክልል በጤናው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ጎብኝቷል።

ዶክተር ቦሪማ በዚሁ ጊዜ በጤናው ዘርፍ አንገብጋቢ እና  ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ለመለየት መምጣታቸውን ገልጸው፤  በቀጣይ  በከተማው አዲስ ለተገነባው የሸንኮር ጤና ጣቢያ አስፈላጊውን የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ  እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡

ድርጅቱ በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ክትባቱን ተደራሽ በማድረግ ሲሰራ መቆየቱንና ይህንንም ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር ቦሪማ አስታውቀዋል፡፡

የሀረሪ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ በበኩላቸው  የአለም የጤና ድርጅት በክልሉ ሲያደርጋቸው የነበሩ ድጋፎች መገምገሙን ገልጸው ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምላሽ ለመስጠት  የሚያስችል 30 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ ለክልሉ ማድረጉን  አስታውሰዋል፡፡

በዚህም በክልሉ 144ሺህ የሚደርሱ ዜጎችን የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡

በዛሬው ውይይትም ድርጅቱ በክልሉ በጤናው ዘርፍ እያደረገ ያለውን ድጋፍ እና አጋርነት አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልፀዋል ፡፡

ልኡካን ቡድኑ በክልሉ በሚገኘው የህይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ቲቺንግ ሪፈራል ሆስፒታል፣  የጀጎል  ሆስፒታል እንዲሁም  የሸንኮር ጤና ጣቢያ የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም