የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከተመድ ዋና ጸሃፊ ጋር ተወያዩ

140
ኒውዮርክ መስከረም 15/2011 በተመድ 73ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከተመድ ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱም ዶክተር ወርቅነህ በኢትዮጵያና በኤርትራ እንዲሁም በኤርትራና ጅቡቲ መካከል የተጀመሩትን የሰላም ሂደቶች ተከትሎ በአፍሪካ ቀንድ አዲስ የሰላም ዘመን መምጣቱን ገልጸዋል ፡፡ ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን ምንጊዜም በትጋት እንደምትሰራ ጠቁመው ተመድ ጥረቱን ለማገዝ ለሚያደርገው ድጋፍ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። ''በቀጠናው ባለፉት ዓመታት የባከነውን የልማት ጊዜ ለማካካስ የሚያስችል እንቅስቃሴ የሚደረግበት ወቅት ላይ እንገኛለን'' ብለዋል፡፡ ዋና ፀሀፊው በበኩላቸው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እየነፈሰ ያለው አዲስ የሰላም አየር የአፍሪካ ቀንድን ሰላማዊ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያፋጥነው ተናግረዋል፡፡ ዋና ጸሀፊው ተመድ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው የቀጠናው ሰላም ለዓለም መረጋጋት ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑንም አውስተዋል፡፡ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ የሚገኙ የሪፎርም ስራዎች አስደናቂ እርምጃዎች መሆናቸውን አውስተው ለውጡን የሚመራው መንግስት ያለውን የአመራር ብስለት እንዲሁም አገሪቱን ለመለወጥ ያለውን ቁርጠኝነት ማድነቃቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም