የከተማ አስተዳደሩ 20 ሚሊዮን ብር በመመደብ የኩላሊት ህሙማን በመንግስት ሆስፒታሎች በነጻ እንዲታከሙ የጀመረው ጥረት የሚበረታታ ነው

109

ጥቅምት 23/2015 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 20 ሚሊዮን ብር በመመደብ የኩላሊት ህሙማን በመንግስት ሆስፒታሎች በነጻ እንዲታከሙ የጀመረው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት አስታወቀ፡፡

በግል የጤና ተቋማት ለሚገለገሉ 4 ሺህ የሚጠጉ ህሙማንን ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቋል፡፡

የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት መንግስት  ሙሉ ወጪውን በመሸፈን በዳግማዊ ምኒሊክ፣ ዘውዲቱና ጳውሎስ  ሆስፒታሎች  የሚሰጠው የኩላሊት እጥበት ህክምና ለበርካታ ህሙማን እፎይታ ሰጥቷል።

ይህን አገልግሎት በማጠናከርም በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ የኩላሊት ህሙማን መፍትሄ ለመስጠት የበለጠ መስራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኩላሊት ህሙማን 20 ሚሊዮን ብር በመመደብ በመንግስት ሆስፒታሎች በነጻ እንዲታከሙ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።

የአስተዳደሩ ድጋፍ  በመንግስት ሆስፒታሎች ለሚገለገሉ ታማሚዎች ብቻ የሚሰጥ በመሆኑ፤ በቀጣይ በግል ጤና ተቋማት የሚገለገሉ 4 ሺህ  የሚጠጉ ህሙማንን ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

ለኩላሊት እጥበት ድጋፋቸውን ይሰጡ ነበሩ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት እገዛቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኩላሊት ንቅለ ተከላ ያደረጉና በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ታካሚዎች መድሃኒቱን ለማግኘት የግድ አዲስ አበባ እንደሚመጡ በመጥቀስ፤ መድሃኒቱ በየክልሉ ሊሰራጭ እንሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ድርጅቱ በከተማ አስተዳደሩ በተሰጠው 1 ሺህ 410 ካሬ ቦታ ላይ ሁለገብ ማዕከል ለመገንባት የሚያስፈልገውን ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ሁሉም ህብረተሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም