የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ምልክት ነው-የመዲናዋ ነዋሪዎች

144

ጥቅምት 23/2015 /ኢዜአ/ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ምልክት መሆኑን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ነዋሪዎቹ የህወሓት የሽብር ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰራዊቱ ላይ የፈጸመውን ግፍ መቼም አንረሳውም ብለዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን አገሪቷን ለ27 ዓመታት ሲበዘብዝ ከኖረ በኋላ በህዝብ ትግል ከስልጣን ተባሮ መቀሌ በመመሸግ የተለያዩ አሻጥሮችን ሲሸርብ ቆይቷል፡፡

ይህ ቡድን ህዝብን በሃይማኖትና በብሔር ስም በማጋጨት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሃይል ጋር በመቀናጀት የአገሪቷን ሰላም ለማደፍረስ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጨረሻ ያለውን የክህደት እርምጃ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሰራዊት ላይ ፈጽሟል፡፡

በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ክህደት የተፈጸመበት ሁለተኛ ዓመትም በነገው ዕለት "ጥቅምት 24ን መቼም አንረሳውም" በሚል ታስቦ ይውላል።

ኢዜአ ካነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች  መካከል አቶ   አብይ ሸዋቀና ና አቶ ጽዋዬ ኪዴ የመከላከያ ሰራዊቱ  በሽብር ቡድኑ ከጀርባ የተፈጸመበት ጥቃት መቼም የማይረሱት ጥቁር ታሪክ መሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪው ቡድን የትግራይ ህዝብን ሲጠብቅ፣ መሰረተ ልማት ሲገነባና በግብርና ስራ አርሶ አደሩን ሲያግዝ በነበረው የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ግፍ ለመናገር የሚከብድ መሆኑንም እንዲሁ።

"አሸባሪው ቡድን መከላከያ ላይ የፈጸመው ጥቃት በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመ ነው " ብለዋል።

ሰራዊቱ የተፈጸመበትን ግፍ ተቋቁሞና ራሱን አደራጅቶ ያስመዘገበው ድልም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያረጋገጠና ለመላው ኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ምልክት መሆኑን ያሳየበት መሆኑን ገልጸዋል።

ሰራዊቱን በአጭር ጊዜ መልሶ በማደራጀት አገር ለማፍረስ የተነሳውን የአሸባሪውን ተልዕኮ ማክሸፉን ጠቅሰዋል።

መስዋዕትነት በመክፈል ያስመዘገበው ድል አገርን ያኮራ ለጠላት ደግሞ ትልቅ መልዕክት ያስተላለፈ እንደነበርም እንዲሁ፡፡

በቀጣይም የሽብር ቡድኑ የፈጸመው አይነት ግፍ በኢትዮጵያ ዳግም እንዳይከሰት ታሪኩን ሰንዶ ለትውልድ ማስተማር እንደሚገባም አንሰተዋል።

አሸባሪው ቡድን ጥቃቱን የፈጸመው ኢትዮጵያን በማፍረስ የአንዳንድ ምዕራባውያንን ተልዕኮ ለማሳካት መሆኑን ጠቁመዋል።

ሰራዊቱን መንካት የኢትዮጵያን ህዝብ መንካት ነው ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ሰራዊቱ ኢትዮጵያን በፅናት የሚጠብቅ በመሆኑ በማንኛውም መንገድ በደጀንነት አብረን እንቆማለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም