በሰቆጣ ና አካባቢው ለ15 ወራት ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት በነገው እለት ጥገና ይጀመራል

132

ሰቆጣ ጥቅምት 23/2015 /ኢዜአ/ በሰቆጣ ና አካባቢው ለ15 ወራት ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት በነገው እለት ጥገና እንደሚጀመር በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሰቆጣ አገልግሎት መስጫ ማእከል አስታወቀ።

የማእከሉ ሃላፊ አቶ ኪሮስ ፈረደ ለኢዜአ እንደገለፁት ሃምሌ16/2013 ዓ/ም ጀምሮ የሰቆጣ ከተማን ጨምሮ የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የሚገኙ ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡን አውስተዋል።

በዚህም ህብረተሰቡ በኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት ለእንግልትና ለኢኮኖሚ ጫና ዳርጎ ነበር ብለዋል።

የህወሃት በፈፀመው ወረራ ምክንያት የሰቆጣ ከተማን ጨምሮ የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ወረዳዎች ከአላማጣ ከሚገኘው ሳብ ስቴሽን ይገኝ የነበረው የኤሌክትሪክ ሃይል ለ15 ወራት ሙሉ በሙሉ መቋረጡን አቶ ኪሮስ ጠቁመዋል።

መንግስት የአላማጣና ኮረም አካባቢዎችን ከህወሃት ነፃ ማውጣቱን ተከትሎ ለ15 ወራት ተቋርጦ የነበረው የሰቆጣ ከተማና የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ወረዳዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማስጀመር በነገው እለት ጥገና እንደሚጀመር ነው አቶ ኪሮስ የተናገሩት።

ከሰቆጣ -ኮረም ድረስ ባለው 29 ቦታዎች ሃይል አስተላላፊ ገመዶች ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል ያሉት አቶ ኪሮስ ጉዳት የደረሰባቸውን የሃይል አስተላላፊ መስመሮችን ለመጠገን የፌደራልና የክልል የኤሌክትሪክ ባለሞያዎች ቡድን በነገው እለት ስራውን ይጀምራል ብለዋል።

ለጥገና የሚያስፈልጉ ግብዓቶች መቅረባቸውንና በአራት ቀናት ውስጥ ጥገናው ይጠናቀቃል ብለዋል።

ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በአግባቡ ሊጠብቅና ሊንከባከቡ እንደሚገባ አቶ ኪሮስ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም