ላሊበላ ከተማ የኤሌክትሪክ ኃይል አገኘች

202

ጥቅምት 23 ቀን 2015 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሀት ቡድን በከፈተው ጦርነት በደረሰ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ውድመት ለረጅም ጊዜ ኤሌክትሪክ የተቋረጠባት የላሊበላ ከተማ በዛሬው ዕለት እንደገና የኤሌክትሪክ ኃይል አግኝታለች፡፡

ከላሊበላ በተጨማሪ ላስታ ወረዳና ሙጃ ከተማም ኤሌክትሪክ ያገኙ ሲሆን፤ እነዚህን አካባቢዎች ተጠቃሚ የሆኑት በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን የአላማጣ - ላሊበላ የ66 ኬ.ቮ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ ሲደረግ የነበረው የጥገና ስራ መጠናቀቁን ተከትሎ መሆኑን የወልዲያ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ወልደሰማያት ገልፀዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም የዲስትሪክቱ ሠራተኞች የጥገና ሥራው በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅና አካባቢዎቹን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ቀንና ማታ ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

እነዚህ አካባቢዎች ከአላማጣ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የሚያገኙ በመሆኑ ለረጅም ጊዜ ኃይል ተቋርጦቦቸው መቆየቱን አስታውሰው፤ በቀጣይ ሰቆጣንና በአካባቢው የሚገኙ ከተሞች የተቋረጠባቸውን አገልግሎት ለመመለስ እንደሚሰራ መግለጻቸውን የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም