የመቱ ከተማና ዙሪያ ወረዳዎች ነዋሪዎች ኦዴፓን በመደገፍ ሰልፍ ወጡ

111
መቱ መስከረም 15/2011 የመቱ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) በቅርቡ ባካሄደው ጉባኤ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በመደገፍ ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ፡፡ በሺህዎች የሚገመቱ ነዋሪዎች በፓርቲው ለተላለፉ ውሳኔዎች ተግባራዊነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሰልፈኞቹ የድጋፍ መልዕክታቸውን ካስተላለፉባቸው መፈክሮች ውስጥ "ኦዴፓ በዘጠነኛው መደበኛ ጉባኤ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች እንደግፋለን!"፣ "አንድነታችንን አጠናክረን የሰላምና የእድገት አደናቃፊዎችን እንታገላለን!"፣ "የብሄር/ብሄረሰቦችን አንድነትና እኩልነት ይበልጥ ለማረጋገጥ ኦዴፓ የሚያደርገውን ጥረት እንደግፋለን!”፣ “ኦዴፓ የአዲሱ ትውልድ ፓርቲ ነው!” የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው ። ከሰልፈኞቹ መካከል ወጣት  አንዋር ጠሀ በሰጠው አስተያየት ኦዴፓ በአዲስ መልክ ራሱን ለለውጥ ማዘጋጀቱ የሚያበረታታ ነው። ወጣት ብልሴ ምትኩ በበኩሏ ፓርቲው  በሁሉም መስኮች እያስመዘገበ ላለው ውጤት አድናቆቷን ገልጻ፣ለፓርቲው ያላትን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጣለች ። "ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ያለንን አንድነትና መቀራረብ ይበልጥ በማሳደግ  አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ  ከፓርቲው ጎን ልንቆም ይገባል " ብላለች ። የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነመራ ቡሊ በመቱ ስታዲዬም በተካሄደው ሰልፍ  ባደረጉት ንግግር ኦዴፓ የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጋራ ይሰራል፡፡ ኦዴፓ በክልሉና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የሚያስችሉትን ወሳኔዎች በዘጠነኛው መደበኛ ጉባዔው አሳልፏል" ብለዋል ። "ፓርቲው በአዲስ መንፈስ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ህዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል " በማለትም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ በድጋፍ ሰልፉ ላይ ወጣቶች፣ሴቶች፣አርሶአደሮች፣ የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ተሳትፈዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም