ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ጫና በፓንአፍሪካኒዝም ላይ የተቃጣ በመሆኑ አፍሪካውያን በጋራ ሊመክቱት ይገባል-ፕሮፌሰር ተይላማ ሚያበይ

114

ጥቅምት 22/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ በተለያየ መንገድ እየደረሰ ያለው ያልተገባ ጫና የፓንአፍሪካኒዝም እንቅሰቃሴን ለመግታት ያለመ በመሆኑ አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ሊመክቱት እንደሚገባ የሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ፓን-አፍሪካኒስት የሆኑት ፕሮፌሰር ተይላማ ሚያበይ ተናገሩ፡፡

በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ጉባኤ ላይ የተገኙት ፕሮፌሰር ተይላማ ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት ናት ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስጠብቃ ከመቆየቷ ባሻገርም ሌሎች የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት አዙሪት ነጻ እንዲወጡ ከፍተኛ ትግል ስታደርግ እንደነበርም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል፡፡

የፓን-አፍሪካኒዝምን እሳቤ ከሌሎች አገራት ጋር በማቀንቀን በምዕራባውያን ጭቆና ስር ለነበሩ ህዝቦች ድምጽ መሆኗንም ነው ያስታወሱት፡፡

ፕሮፌሰሩ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አገራት ህዝቦች ነጻነትና እኩልነት ብዙ ዋጋ የከፈለች መሆኗን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት የገጠማትን ፈተና በድል እንድትወጣ ሁሉም የአፍሪካ አገራት ከጎኗ ሊቆሙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ለአፍሪካ አገራት ህልውና እና እድገት አስፈላጊ መሆኑንም ፕሮፌሰር ተይላማ ሚያበይ ገልጸዋል፡፡

የፓን-አፍሪካን ራዕይና እሳቤ እንዲሁም ለአህጉሪቱ ስለሚያበረክተው ጠቀሜታ ለአዲሱ ትውልድ ማስተዋወቅ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ከአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ወጣቶችን በማሰባሰብ የፓን አፍሪካኒዝም ራዕይን ለማጠናከር፣ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እና በአፍሪካ ወጣቶች መካከል ያለውን ወንድማማችነት ለማጠናከር ሰፊ ስራ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

"የኢትዮጵያ የነጻነት ምልክትነት ለአፍሪካ አህጉር ብቻ ሳይሆን ለዓለም ጭምር ነው" በማለትም ኢትዮጵያ በፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ ላይ እየተጫወተች ያለውን ታላቅ ሚና ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቅኝ አገዛዝን ያሸነፈችበት ቁልፍ ምክንያት ዳር እስከ ዳር ህዝቦቿ አንድ ላይ በመነሳታቸው ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ መከፋፈል አፍሪካ እንድትወረር ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

"ከተከፋፈልን ደካሞች እንሆናለን ከተባበርን ደግሞ በእኛ ላይ የሚመጡ ኃይሎች አሳፍረን መመለስ እንችላለን" ሲሉም ሃሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

"ምዕራባውያን በአፍሪካ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡት ለማዳከም ስለሚፈልጉ ነው" ያሉት ፕሮፌሰሩ የአፍሪካውያን እጣ ፈንታ አንድ በመሆኑ አንድነታቸውን አስጠብቀው ጣልቃ ገብነትን በጋራ መመከት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

ለአፍሪካውያን ችግር መፍትሔው በአፍሪካውያን እጅ ነው፤ እናም ይህን መፍትሔ ለማምጣት መተባበር እና አንድነታችንን ማጠናከር ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ፓን-አፍሪካኒዝም ችግሮችን ለመፍታት በአፍሪካውያን መካከል መተባበር እንዲመጣ የሚያደርግ ዋና መንገድ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም