የትራማዶል መድሃኒት በልዩ የሃኪም ትእዛዝ ብቻ እንዲሸጥ ተወሰነ - ኢዜአ አማርኛ
የትራማዶል መድሃኒት በልዩ የሃኪም ትእዛዝ ብቻ እንዲሸጥ ተወሰነ
ጥቅምት 22/2015 (ኢዜአ) የትራማዶል መድሃኒት ከልዩ የሀኪም ትእዛዝ ውጭ መሸጥ እንደማይቻል የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ባለስልጣኑ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ከጤና ባለሙያ ትእዛዝ ውጭ በርካታ አፍላ ወጣቶች ለህመም ማስታገሻነት በሚል መድሃኒቱን ያለአግባብ እንደሚጠቀሙት መረጃ እንደደረሰው አስታውቋል።
የባለስልጣኑ የመድሃኒቶች ደህንነት ዳይሬክተር አስናቀች አለሙ እንዳሉት ትራማዶል ለአዕምሮ ጤና ህሙማንና እንደ ካንሰር ላሉ በሽታዎች ለማስታገሻነት የሚሰጥ መድሃኒት ነው፡፡
ባለስልጣኑ የመድሃኒቱን ሱስ የሚያስይዝ ባህሪ ከግምት ውስጥ በማስገባት ያለማዘዣ ከሚታዘዙ መድሃኒቶች ዝርዝር ውስጥ ለማውጣት የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።
የመድሃኒቱን አጠቃቀም በሚመለከት በተደረገ ጥናትና ዳሰሳ መድሃኒቱ በተለይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አካባቢ እየተዘወተረና ሱስ እየሆነ መምጣቱ መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡
ይህም በተለይ በወጣቶች ላይ ከፍተኛ የማህበራዊ ቀውስ እንደሚያስከትል ነው የጠቆሙት፡፡
በመሆኑም መድሃኒቱ በልዩ የሀኪም ትእዛዝ ብቻ ወደ ሚሰጡ መድሀኒቶች ምድብ እንዲካተት መደረጉን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የመድሃኒቱ ማዘዣ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግበታል ነው ያሉት፡፡
ባለስልጣኑ መድሃኒቱን አለአግባብ የሚሸጡ፣ የሚያሰራጩ እና የሚጠቀሙ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም ነው ባለስልጣኑ ያስታወቀው።