የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት የአንድ ወቅት ዝግጅት ማድመቂያ ብቻ መሆን የለበትም ተባለ

45
አዲስ አበባ መስከረም 15/2011 የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት የአንድ ወቅት ዝግጅት ማድመቂያ ብቻ ሳይሆን የየዕለት ተግባር መሆን እንዳለበት የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ገለጸ። አስተዳደሩ "ለወገኔ እኔም አለሁ" በሚል መሪ ሀሳብ በክረምቱ መርሃ ግብር ሲያከናውን የነበረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዛሬ ማጠቃለያ ሰጥቷል። በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከታራሚ እናቶች ጋር ላሉ 23 ህፃናት ሙሉ ልብስና ለሴት ታራሚዎች የተለያዩ አልባሳት አበርክቷል። በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማም ወረዳ 7 ለአንድ የ 75 ዓመት አዛውንት ግምቱ 75 ሺህ ብር በሚሆን የገንዘብ ወጭ ቤታቸው ታድሶ እንዲረከቡ ተደርጓል። በተጨማሪም አዛውንቱ የራሳቸው ገቢና ረዳት የሌላቸው በመሆኑ በእድሜ ዘመናቸው የሚያስፈልጋቸውን የህከምና ወጭ ለመሸፈን የማረሚያ ቤት አስተዳደሩ ቃል ገብቶላቸዋል። የፌደራል ማረሚያ ቤት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል አባሶ እንዳሉት፤ ማረሚያ ቤቱ በክረምቱ መርሃ ክብር ሲያከናውነው የነበረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዚህ የሚቆም አይደለም። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጡ ወቅት ተብቆ የሚከናወን የዘመቻ ስራ ሳይሆን "ቀጣይነት ያለውና የየዕለት ተግባር መሆን ይኖርበታል" ብለዋል። ለዚህም የፌደራል ማረሚያ ቤት አስተዳደር በታራሚዎችና በአስተዳደር ሰራተኞች መካከል አንዱ አንዱን ማገዝ  የሚችሉበት ቅርርብ መፍጠር ይገባልም ብለዋል። ከቃሊቲ ከፍተኛ የጥበቃ ማረፊያ ቤት አስተዳደርና የሴቶች ማረፊያና ማረሚያ ቤት አስተዳደር ጋር በመተባበር ያከናወኑት ቤት የማደስ እንዲሁም ለታራሚዎች የአልባሳትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ነዋሪ የሆኑት የ 75 ዓመቱ አዛውንት አቶ ደያሳ ደገፉ ክረምት በፍሳሽ ምክንያት ለዝናብና ብርድ ተጋልጠው ሲቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል። ረዳት ዘመድ እንደሌላቸውና በጎረቤቶቻቸው መልካም ፈቃድ እርዳታ ሲያገኙ እንደነበር ገልጸው፤ አሁን መንግስት ያደረገላቸውን ድጋፍ "የእድሜ ዘመኔ ደስታ" ሲሉ በሲቃ ገልጸውታል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም