ፕሬዝዳንቱ የአዲሲቱ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ልዑክን አነጋገሩ

61
አዲስ አበባ መስከረም 15/2011 የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በአቶ ኦባንግ ሜቶን የሚመራውን የአዲሲቱ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ልዑካንን አነጋገሩ። ወጣቶች በመከባበርና በመደጋጋፍ ሰላማዊና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ጥሪ አቅርበዋል። አቶ ኦቦንግ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ሁላችንም በአንድ አገር ጥላ ስር የምንኖር ወንድማማች ህዝቦች መሆናችንን ተገንዝበን ችግሮችን በሃይል ከመፍታት ይልቅ መነጋገርን ማስቀደም አለብን። የኢትዮጵያ እድገት መጻኢ ተስፋዎች ወጣቶች መሆናቸውን ገለጸው፤ ወጣቶች እርስ በርስ በመከባበርና በመደጋገፍ ይህንን ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። "አንድ እጽዋት ብቻውን የአትክልት ቦታ ሊሆን አይችልም" ያሉት አቶ ኦቦንግ፤ ትውልዱ  ለጋራ እሴትና አንድነት ትኩረት መስጠት እንዳለበት ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል። እርሳቸውን ጨምሮ የንቅናቄው አባላቶች በቀጣይ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ቢሮ በመክፈት የወጣቶችን አብሮነት የሚያጠናክሩ ስራዎች ለማከናወን ማቀዳቸውን ገልጸዋል። በፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የኮሙኒኬሽንና ፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት በበኩላቸው ንቅናቄው ወጣቶች እርስ በርስ በመዋደድ ለአገራቸው እድገት አሻራ እንዲያስቀምጡ አበክሮ እንዲሰራ ፕሬዚዳንቱ  ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። አቶ ኦባንግ ከረዥም ዓመታት በኋላ ወደ አገራቸው መጥተው የተመለከቱትን ትክክለኛ ገጽታ ለሌሎች ማስገንዘብ እንዳለባቸው ፕሬዚዳንቱ መናገራቸውን ጠቁመዋል። ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ አቶ ኦባንግን ጨምሮ የንቅናቄው አባላት በዕቅድ ለያዙት በጎ ተግባር መሳካት አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር  እንደሚያደርጉ መግለጻቸውንም አውስተዋል። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ከትጥቅ ሃይል የጸዳና ፖለቲካዊ ያልሆነ ለዜጎች ፍትህ፣ እኩልነት፣ ነጻነትና ሰብዓዊ መብት መከበር የሚሰራ ንቅናቄ ነው። ንቅናቄው እአአ በ2008 የተመሰረተ ሲሆን፤ "ሁሉም ነጻ ሳይሆን ማንም ብቻውን ነጻ ሊሆን አይችልም" በሚል መሪ ሃሳብ እየሰራ ይገኛል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም