ህብረት ስራ ማህበራት ባንኮች ባልተከፈቱባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች የፋይናንስ ተደራሽነትን በማስፋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው - ኮሚሽኑ

204

ጥቅምት 21/2015 (ኢዜአ) የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት ባንኮች ባልተከፈቱባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች የፋይናንስ ተደራሽነትን በማስፋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ኀብረት ሥራ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ "የቁጠባና ብድር ኀብረት ሥራ ማኀበራት ለተጠናከረ ፋይናንስ አቅም" በሚል መሪ ሃሳብ ዓለም አቀፉን የገንዘብ ቁጠባና ብድር የህብረት ሥራ ቀን አክብሯል።       

በዓለም ለ74ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው የገንዘብ ቁጠባና ብድር የህብረት ሥራ ቀን ግንዛቤ ለመፍጠርና ዘርፉን ለማጎልበት ያለመ መሆኑ ታውቋል።      

የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው የባንክ አገልግሎት በሌለበት አካባቢ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ዓይነተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው።

በተለይ ትልልቅ የፋይናንስ ተቋማትን በሁሉም አካባቢ መክፈት እንደማይቻል አንስተው፤የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት ይህንን በመሸፈን ላይ ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በባንክና በሌሎች መደበኛ የፋይናንስ ተቋማት የሂሳብ ደብተር ከፍተው የሚጠቀሙ ዜጎች ከ35 በመቶ አያልፉም ያሉት ኮሚሽነሯ አሁንም የበለጠ ሊሰራ እንደሚገባ አመላካች ነው ብለዋል።  

ኮሚሽኑ የገንዘብ ብድርና ኅብረት ሥራ ማህበራትን በየክልሎች ለማስፋትና ለማጠናከር ጥረቶች በማድረግ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።    

በዚህም 22 ሺህ 485 የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት፣ 133 የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ዩኒየኖች እንዲሁም 2 የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ፌደሬሽኖች ማቋቋሙን አስረድተዋል።     

ከ6 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ አባላት ማፍራት መቻሉን ገልጸው፤ከ36 ነጥብ 896 ቢሊዮን ብር በላይ ቁጠባና ዕጣ ማሰባሰብ እንደተቻለም አብራርተዋል።   

ዘርፉ ለፋይናንስ ማደግ የራሱን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ሲሆን በ2014 ዓ.ም ብቻ የ9 ቢሊዮን ብር ብድር ስርጭት ተከናውኗል ብለዋል።    

የገንዘብ ቁጠባና ብድር ተቋማት የሚያበረክቱትን አገራዊ አስተዋጽኦ የበለጠ ለማሳደግ ኮሚሽኑ ህጋዊ አሰራሮችን የማውጣትና የማሻሻል ስራዎች ላይ ትኩረት ማድረጉንም ገልጸዋል።  

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ፤ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት አገልግሎታቸውን ለማሻሻል ቴክኖሎጂን መጠቀም ይገባቸዋል ብለዋል።  

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የሚመራ የፋይናንስ ተደራሽነት ስቲሪንግ ኮሚቴ በማቋቋም የፋይናንስ ተቋማት የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ እንዳለም ጠቁመዋል።

ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ማህበራትን በማጠናከር አገልግሎታቸውን በዲጂታል የታገዘ እንዲያደርጉ የሚያስችል ስልጠና የሚሰጥበት አሰራር መዘርጋቱን አስታውቀዋል።

የአዋጭ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ኅብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ ዘሪሁን ሸለመ በበኩላቸው፤በአገሪቱ የቁጠባ ባህል እንዲያድግ እየሰራን ነው ብለዋል።   

ህብረት ስራ ማህበሩ ለእናቶች፣ ለሴቶች እና ለወጣቶች ብድር እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ባንኮች በሌሉበት አካባቢ አገልግሎቱን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።   

የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት የዜጎችን ህይወት በመቀየር ረገድ ያላቸው ፋይዳ ከፍ ያለ በመሆኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም