ሀገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት ለሚሰሩ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች አስፈላጊው እገዛ ይደረጋል…የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

148

ጥቅምት 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሀገራዊ የልማት ግቦች ስኬታማነት ላይ አተኩረው የሚንቀሳቀሱ ተቋማትን የሚዲያና ኮሚኒኬሽን አቅም ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።

ተቋሙ በአዋጅ ቁጥር 1115/2011 ሲቋቋም ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች መካከል በሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሙያዊ ስልጠናዎችን አደራጅቶ መስጠት ይገኝበታል።

በዚሁ መሰረት ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባሙያዎች ፍላጎታቸውን ያማከለ ሰልጠና ሲሰጥ ቆቷል።

በተያዘው በጀት አመትም በመጀመሪያ ዙር ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በሚዲያና ኮሚኒኬሽን ዘርፍ የሚሰጠውን ስልጠና ዛሬ ጀምሯል።

በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ እንደተናገሩት ኢዜአ ለሀገራዊ የልማት ግቦች ስኬታማነት ከሚሰሩ የኮሚኒኬሽንና ሌሎች ተቋማት ጋር በሚዲያና ኮሚኒኬሽን ዘርፍ እየሰራ ነው።

ስልጠናዎቹን ከየተቋማቱ ተልእኮና ግብ ጋር በማስተሳሰር ለውጥ ለመምጣት በሚያስችል መልኩ እንደሚሰጡ አንስተው ተቋማት ዋና ዋና ተግባራቸውን የማስተዋወቅና ግንዛቤ የመፍጠር ስራን አስፈላጊነት ሊረዱ እንደሚገባም አመላክተዋል።

“አሁን የተሰናዳው ስልጠናም ስራን ከተግባቦት ጋር በማጣመር የተቋማትን አቅም ለማጎልበት ያለመ ነው” ሲሉ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

በኢዜአ የሥልጠና ምክርና ምርም ማዕከል ኃላፊ አቶ አብዱራህማን ናስር በበኩላቸው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎችና ባሙያዎች ፍላጎታቸውን ያማከለ ሰልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህኛውም ዙር የስልጠናው ተሳታፊዎች በዘርፉ ባለሙያዎች አማካኝነት በሚቀርበው በንድፈ ሃሳብና በተግባር የተደገፈ ስልጠና የተሻለ ክህሎት የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱንነው የጠቀሱት።

ይሄንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሰልጣኞች የተቋማቸውን የተግባቦትና ህዝብ ግንኙነት ስራዎችን ለማሳደግ የሚረዳቸውን ክህሎትና ልምድ ከአንጋፋው ተቋም ለመውሰድ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መክረዋል።

ኢዜአ ባለፈው በጀት ዓመት የመከላከያ ሚኒስቴርና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን ጨምሮ ለ14 ተቋማት በሚዲያና ኮሚኒኬሽን ዘርፍ ስልጠና የሰጠ ሲሆን በዚህም አመት ለሰባት ተቋማት ባለሙያዎች መሰል ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም