ከአላማጣ እስከ ቆቦ የሚከናወነው የመካከለኛ ኤሌክትሪክ መስመር ጥገና ሥራ ተጠናቀቀ

240

ጥቅምት 21/ 2015 (ኢዜአ ) በአሸባሪው የህወሃት ቡድን የወደመውን ከአላማጣ እስከ ቆቦ ያለው የመካከለኛ ኤሌክትሪክ መስመር የጥገና ሥራ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ ተገለጸ።

የወልዲያ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ወልደ ሰማያት እንደገለጹት የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ጥገናው በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የተቋሙ ሠራተኞች ቀንና ማታ በከፍተኛ ትጋት ስራውን አከናውነዋል።

አቶ ሽመልስ አክለውም ከአላማጣ እስከ ቆቦ ያለው የመካከለኛ መስመር የጥገና ስራ በአሁን ወቅት መቶ በመቶ መጠናቀቁና አካባቢው እንደገና የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ከአስተዳደሩ ጋር በመተባበር የዛፍ ቅርንጫፎችን የማፅዳት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የዛፍ ቅርንጫፎችን የማፅዳት ሥራው እንደተጠናቀቀ ቆቦን ጨምሮ በዚህ መስመር ኤሌክትሪክ የሚያገኙ አካባቢዎች እንደገና የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚያገኙም ጠቁመዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አያይዘውም ከአላማጣ እስከ ላሊበላ የተዘረጋው የ66 ኪ.ቮ የትራንስሚሽን መስመር የጥገና ሥራ 90 በመቶ መጠናቀቁንም ተናግረዋል፡፡

ይህም መስመር ቶሎ በማጠናቀቅ ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ ሠራተኞች አሁንም ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ የጥገና ሥራ እስከ 50 የሚደርሱ የዲስትሪክቱ ሠራተኞች እየተሳተፉበት እንደሚገኝና ከአላማጣ እስከ ቆቦ ያለው የመካከለኛ መስመር ጥገና በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም