የኢትዮጵያ ባህር ትራንዚትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን ወደግል ለማዞር ጥናት እየተካሄደ ነው

66
አዲስ አበባ  መስከረም 15/2011 የኢትዮጵያ ባህር ትራንዚትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን ወደ ግል ይዞታ ለማዞር በድርጅቱ ሃብትና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጥናት እየተደረገ መሆኑ ተጠቆመ። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከወቅቱ ጋር አብሮ የሚሄድ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ግንቦት ወር ላይ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የመንግስት የልማት ድርጅቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ወደ ግል እንዲዛወሩ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በዚህም ወደ ግል እንዲዛወሩ ከተባሉ የመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ባህር ትራንዚትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሙሉ በሙሉ አልያም በከፊል ወደ ግል ይዞታ የሚቀየርበትን ሁኔታ ለመወሰን ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሮባ መገርሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ድርጅቱን ወደ ግል ይዞታ ለማዞር የሚያስፈልጉ የሃብት ጥናት እንዲሁም የህግና የስምምነት ፓኬጆችን የማዘጋጀት ስራ እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በቀጣይ በመንግስት በኩል ከተቋቋመው የአማካሪ ቦርድ አማካኝነት የሚሰጠውን አቅጣጫ በመውሰድ በውስጥ አቅም ሊሰሩ የሚችሉ ስራዎችን የማከናወን ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል። ይህም ሌላ ተጨማሪ አቅም እና ሰፊ የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ታምኖበታልም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።     ውሳኔውን ተከትሎ የልማት ድርጅቶቹን ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ወደግሉ ዘርፍ ለማዛወር የሚያማክር ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል። ከማሻሻያዎቹ መካከል የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የአክስዮን ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያስችለው ውሳኔ ተጠቃሽ ነው። በመንግስት ይዞታ ሥር ያሉና በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትም ሆነ በግንባታ ላይ የሚገኙ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴል እና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንደሚተላለፉ ውሳኔ ከተላለፈባቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ። እንዲሁም የኢትዮ-ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው አክሲዮን ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፉ መወሰኑ ይታወሳል። ውሳኔው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለረጅም ጊዜያት በአገራቸው ልማት ለመሰማራት ያላቸውን ምኞት የሚያረጋግጥ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም