የመስቀል በዓል በሰላም እንዲከበር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዝግጅቱን አጠናቋል

68
አዲስ አበባ መስከረም 15/2011 የደመራና የመስቀል በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ለማስቻል አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚከበረውን የመስቀል በዓል ኢትዮጵያዊያን የባህላቸው፣ የትውፊታቸውና የማኅበራዊ ዕሴቶታቸው አካል አድርገው ያከብሩታል። በዓሉ እንደየብሄረሰቡ ፣ አካባቢና ቋንቋ የተለያየ ስያሜ አለው፤ በሃድያ፣ በወላይታ፣ በዳውሮና ጋሞ "መስቀላ"፤ በከምባታ "መሳላ"፤ በየም "ሄቦ" በጉራጌ "መስቀር"፤ በኦሮሞ "ጉባ" ወይም "መስቀላ"፤ በከፊቾ እና ሻኬቾ "መሽቀሮ" በመባል ሲታወቅ በአማራና ትግራይ ክልሎች ደግሞ መስቀል ይባላል። በተለይ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በዓሉ የራሱ ትርጓሜ ያለው ቢሆንም ከሃይማኖታዊ ክንዋኔው ባሻገር ባህላዊ ገፅታውን የሚያከብሩት የህብረተሰብ ክፍሎች በርካቶች ናቸው። እንደ ዕንቁጣጣሽ፣ ጥምቀትና ልደት ያሉ ብሔራዊና መንፈሳዊ በዓላት ሁሉ የመስቀል በዓል አከባበር መንፈሳዊነቱና ባህላዊ ገጽታውን ሳይለውጥ ለዘመናት የዘለቀም ነው። የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ከአከባበር ሥርዓቱ ባሻገር የቱሪስት መስህብ በመሆን ለአገር ኢኮኖሚና ገጽታ ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ እያደገ መምጣቱም ይታወቃል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ በዓሉ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ በሠላም እንዲከበር ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ነው የገለጹት። ህብረተሰቡም በዓሉ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ከጸጥታ አካላት ጋር እንዲተባበርም ጥሪ አቅርበዋል። የመስቀል በዓል አከባበር በ2006 ዓ.ም በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ በተካሄደው 8ኛው የተባበሩት መንግስታት የሳይንስ የትምህርትና ባህል ማዕከል /ዩኔስኮ/ ጉባኤ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ነው። ነገ በሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በርካታ የክርስትና እምነት ተከታዮችና አባቶች፣ የውጭ አገራት ጎብኚዎች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶችና ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኀን እንደሚታደሙ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም