ትውልዱ በትምህርት የሚያገኘውን ዕውቀትና ክህሎት ለሕዝባዊ አገልግሎትና ለአገር እድገት ለማዋል መሥራት አለበት- ዶክተር ሊያ ታደሰ

198

ጥቅምት 19/2015/ኢዜአ/ የአሁኑ ትውልድ በትምህርት የሚያገኘውን ዕውቀትና ክህሎት ለሕዝባዊ አገልግሎትና ለአገር እድገት ለማዋል ሊሰራ እንደሚገባ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 298 የሕክምና ዶክተሮችን በዛሬው እለት አስመርቋል።

በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ተገኝተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ በብዙ ውጣ-ውረድ አልፈው ለዚህ ክብር የበቁትን ተመራቂዎች እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ደስታቸውን ተጋርተዋል።

የጤና ሥርዓቱ በርካታ ለውጦችን እያስመዘገበ ቢሆንም ጥራት ያለው ሕክምና ከመስጠት አኳያ ያልተቀረፉ ተግዳሮቶች እንዳሉበት ተናግረዋል።

ይህንኑ ክፍተት ለመሙላት በሚደረገው እንቅስቃሴ ተመራቂ የሕክምና ባለሙያዎቹ የገቡትን ቃል-ኪዳን በማክበር የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ለአንድ ሀገር እድገትና ለውጥ የተማረ የሰው ኃይል ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመናገር ተመራቂዎቹ በቀሰሙት ዕውቀት በመታገዝ ማኅበረሰቡን በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው፤ ከፍተኛ ትዕግስትና ጥረት የሚጠይቀውን የሕክምና ሙያ በስኬት በማጠናቀቅ ለምረቃ ለበቁት ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 72 ዓመታት የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝና ላለፉት 50 ዓመታት በሕክምናው ዘርፍ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ጥራት ያለው የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም  ገልጸዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል ለቻሞ ላምባሞ እና ማህደር ንጉሴ 3 ነጥብ 91 ነጥብ በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልመዋል።

ተመራቂዎቹ ሀገራቸውና ሕዝባቸውን በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ከዛሬ ተመራቂዎች መካከል 184 ወንዶች ሲሆኑ 114ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሕክምና ተማሪዎችን አስተምሮ ሲያስመርቅ ዘንድሮ ለ51ኛ ጊዜ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም