በኢትዮጵያ የመድሃኒት አቅርቦት ችግርን የሚፈታ ''ግዴታ የተገባለት አቅርቦት '' የተሰኘ አሰራር ወደ ሙሉ ትግብራ ሊገባ ነው

272

ጥቅምት 19/2015/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ በጤና ተቋማት የሚከሰተውን የመድሃኒት አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣምን የሚፈታ ''ግዴታ የተገባለት አቅርቦት '' የተሰኘ አሰራር በተያዘው ዓመት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ለመንግስት የጤና ተቋማት መድኃኒቶችንና የህክምና መሳሪያዎች ያቀርባል።

ከአምስት ሺህ ለሚበልጡ ጤና ተቋማትም  በየዓመቱ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድሃኒቶችና የህክምና ግብዓቶች  እንደሚያቀርብ  የአገልግሎቱ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በጤና ተቋማት የሚቀርቡ የመድሃኒት ጥያቄዎች በጥናት ላይ ያልተመሰረቱና ትክክለኛ የፍላጎት መጠንን የሚገልጹ ባለመሆናቸው አንዳንዶች ላይ እጥረት ሲከሰት ያለፍላጎት በብዛት ወደገበያው የሚቀርቡም አሉ።

ይህ ደግሞ የመድሃኒት ብክነትና እጥረትን ከማስከተሉም ባለፈ ማህበረሰቡ ማግኘት ያለበትን የህክምና አገልግሎት በአግባቡ ሳያገኝ ይቀራል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር  ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ እንዳሉት ችግሩን ለመፍታት  ባለፈው ዓመት የተጀመረው "ግዴታ የተገባለት አቅርቦት" በተያዘው ዓመት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል።

ይህም የጤና ተቋማት በጥናት ላይ በተመሰረተና በትክክለኛ ፍላጎታቸው ልክ የመድሃኒትና የህክምና ግብዓቶችን ወስደው ለህብረተሰቡ በአግባቡ ተደራሽ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ መሆኑን አስረድተዋል።

አሰራሩ ባለፈው ዓመት በ32 ሆስፒታሎች በሙከራ ደረጃ ሲተገበር የቆዬ ሲሆን ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል ነው ያሉት።

ተሞክሮውን ወደ ሌሎቹ በማስፋት የመድሃኒት አቅርቦትና  አለመጣጣምን ለመፍታት እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ አሰራሩን ለመተግበር ከሁሉም የጤና ተቋማት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

በተለይ ተቋማቱ የመድሃኒት ልየታና ምጣኔ በመስራት በጀት አስቀድመው በመያዝ  ሙሉ በመሉ የመድሃኒት ፍላጎታቸውን እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በተለያዩ ስያሜዎች በመጠራት ላለፉት 75 ዓመታት መድኃኒቶችን፣ የህክምና መሳሪያዎች ለጤና ተቋማት  በማቅረብ ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም