ድርጅቱ በአማራ ክልል ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜት እያካሄደ መሆኑን ገለጸ

206

ባህርዳር ጥቅምት 19/2015(ኢዜአ) የአማራ ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።

ሰሞኑን የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ አካባቢዎች የግብርና ምርት እንቅስቃሴን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የአማራ ምርጥ ዘር ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ጀምበሬ ወርቅነህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ድርጅቱ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ እየመጣ ያለውን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል በመኸር የምርጥ ዘር ብዜት እየተካሄደ ይገኛል።

በዚህም 4 ሺህ 787 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የሰብል ዝርያዎች የምርጥ ዘር ብዜት እየተካሄደ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በዘንድሮው መኸርም በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ አኩሪ አተርና ሌሎች ሰብሎች ከተሸፈነው መሬት ላይ ከ104 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የበጋ መስኖ ልማት እየተስፋፋ ከመምጣቱ አንጻር የሚፈለገውን ግብአት ለማሟላት ድርጅቱ 24 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ማግኘት ከቻለ ከ680 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር በማምረት የክልሉን ምርጥ ዘር ፍላጎት ሙሉ በሙሉ መሸፈን ይቻላል ብለዋል።

በተመሳሳይ 'ኢትዮ አግሪ ሴፍት' የተሰኘ ድርጅትም በምዕራብ ጎጃም ዞን ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜት እያካሄድ ይገኛል።

በ'ኢትዮ አግሪ ሴፍት' የላይኛው ብር እርሻ ልማት ስራ አስኪያጅ አቶ ውድአለው መኮነን እንደገለጹት ከዚህ ውስጥ ከ792 ሄክታር የሚጠጋው መሬት በስንዴ ምርጥ ዘር የተሸፈነ ሲሆን 234 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ደግሞ የበቆሎ ምርጥ ዘር ተሸፍኗል።

ቀሪው በአኩሪ አተር፣ ሱፍና ሌሎች ሰብሎች መሸፈኑን ጠቁመው ይህም የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረትን በመቅረፍ የክልሉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ትልቅ አስታዋፅኦ አለው ብለዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው የክልሉን የምርጥ ዘር እጥረት ለመቅረፍ ለዘር ብዜት የሚያስፈልግ መሬት እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።

እስካሁን በተሰራው ስራ ለመጀመሪያ ጊዜ ከክልሉ 5 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል ውጤት ተገኝቷል።

በአማራ ክልል በዘንድሮው መኸር በስንዴ ከለማው ከ830 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከ32 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም