የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኤሌክትሪክ ንዑስ ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ሥራ ተጀመረ

80

ምዕራብ ጎጃም (ኢዜአ) ጥቅምት 18/2015 የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጭ የሚገነባውን የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኤሌክትሪክ ንዑስ ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ሥራን ዛሬ አስጀመሩ።

በርዕሰ መስተዳድሩ የተመራው የክልሉ ከፍተኛ አመራር ቡድን ከማከፋፈያ ጣቢያው የግንባታ ማስጀመሪያ ሥነስርአት በኋላ የቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝቷል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኛቸው አስረስ እንደገለጹት፣ ፓርኩ የአርሶ አደሩን ምርት በግብአትነት በመጠቀም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማስፋት ታቅዶ የተቋቋመ ነው።

ይሁን እንጂ የኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት ባለሃብቶች በሚፈለገው መጠን ወደፓርኩ እንዳይገቡና የገቡትም በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ገልፀዋል።

ችግሩ እንዲፈታ በክልሉ እና በፌደራል መንግስት በተደረገ ጥረት በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጭ የንዑስ ማከፋፈያ ጣቢያው የግንባታ ሥራ ዛሬ መጀመሩን ተናግረዋል።

አቶ ዳኛቸው እንዳሉት ባለ 230 ኬቢ ማክፋፈያ ጣቢያው በ9 ነጥብ 9 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ነው።

የማከፋፈያ ጣቢያውን ግንባታ በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ወደሥራ ለማስገባት ሥራው በሁለት ሥራ ተቋራጮች እንዲከናወን መደረጉንም አስረድተዋል።

የግንባታ ሥራው የኤሌክትሪክ ሀይልን ከዋናው መስመር ወደንዑስ ማከፋፈያ ጣቢያ ለማድረስ የሚያስችል የ90 ኪሎ ሜትር መስመር ዝርጋታን እንደሚያካትትም አስረድተዋል።

"የግንባታ ሥራው ሲጠናቀቅም በፓርኩ ውስጥ ሥራ ለጀመሩና አዲስ ለሚገቡ ኢንዱስትሪዎች በቂ ሃይል ለማቅረብ ይቻላል " ሲሉ የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኛቸው ተናግረዋል።

የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ 264 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑ የሚታወቅ ነው።

በፓርኩ ጉብኝትና በጣቢያው የግንባታ ማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት ላይ ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም