በአፋር 59 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት ሥራ ተጀምሯል

69
ሰመራ /ደንረብርሀን መስከረም 15/2011 በአፋር ክልል በበጋው ወራት ከ59 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የማልማት ሥራ መጀመሩን የክልሉ አርብቶ አደርና ግብርና ልማት ቢሮ አስታወቀ። በሌላ በኩል በመኽር ወቅት በኩታ ገጠም ማሳ የዘሩትን ማሽላ እየተንከባከቡ መሆናቸውን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አርሶ አደሮች ገልፀዋል። በቢሮው የኤክስቴንሽን ሥራ ሂደት ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ አህመድ ያሲን ለኢዜአ እንደገለጹት በ27 ወረዳዎች በተጀመረው የመስኖ ልማት እስካሁን 15 ሺህ ሄክታሩ ታርሶ በዘር ተሸፍኗል። “በቆሎ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ማሽላ፣ቲማቲምና ሽንኩርት በመስኖ እየለሙ ካሉ ሰብልና የጓሮ አትክልቶች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው” ብለዋል። የመስኖ ልማቱ የአዋሽን ወንዝ በባህላዊና ዘመናዊ መንገድ በመጥለፍና ሌሎች የውሃ አማራጮችን በመጠቀም የሚካሄድ እንደሆነም ተናግረዋል። አቶ አህመድ እንዳሉት በዚህ ዓመት በመስኖ የሚለማው መሬት ባለፈው ዓመት ከለማው በ1 ሺህ 600 ሄክታር ብልጫ አለው። ለተሳታፊ ከፊል አርብቶ አደሮች 420 ኩታንታል የበቆሎ፣ ስንዴ፣ ማሾና የጓሮ አትክልት ምርጥ ዘር ቀርቦ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ተናግረዋል። እየለማ ካለው መሬት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል። የአይሳኢታ ወረዳ የበርጋ ቀበሌ ከፊል አርብቶ አደር አቶ አሊ ከቢር በ2 ሄክታር መሬት በቆሎና የጓሮ አትክልት በመስኖ እያለሙ መሆናቸውን ገልፀዋል። በአፋምቦ ወረዳ የሁመዶይታ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዳውድ ጀማል በኩላቸው የመስኖ ልማት ሥራቸውን ለመጀመር የማሳ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በሌላ በኩል በኩታ ገጠም ማሳ ላይ በመኸር ወቅት የዘሩትን ማሽላ እየተንከባከቡ መሆናቸውን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አርሶ አደሮች ገልፀዋል። በዞኑ የአርጡማ ፉርሲ ወረዳ የጃራ ቀጨማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሁሴን ሀሰን ለኢዜአ እንደገለጹት ማሳቸውን ከአረምና ከተባይ ነጻ ለማድረግ እየተንከባከቡ ይገኛሉ። በኩታገጠም ከዘሩት ግማሽ ሄክታር ማሳ 15 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ አመላክተዋል። አርሶ አደር መሃመድ ሀሰን በበኩላቸው በምርተ ወቅቱ በኩታገጠም ማሳ በመዝራታቸውና በቡድን በመስራታቸው  ለተባይ መከላከልና ለአረም ስራ ያባክኑት የነበረውን ጊዜና ጉልበት ቀንሶላቸዋል። “ከአንድ ሄክታር ማሳ 25 ኩንታል ማሽላ አገኛለሁ ብዬ እገምታለሁ” ብለዋል። የዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ተሾመ ገለቱ እንደገለጹት በዞኑ 19 ሺህ 424 ሄክታር ኩታገጠም ማሳ በመኸር እርሻ በማሽላ ሰብል ተሸፍኗል። እንደ ቡድን መሪው ገለጻ 11 ሺህ 659 አርሶ አደሮች በመኸሩ እርሻ እየተሳተፉ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም