የአሣ ልማት ኮሚቴ መቋቋም ሃብቱን በአግባቡ ለማልማትና ለመጠቀም ያስችላል

86
ሰቆጣ  መስከረም 15/2011 የተከዜ ሰው ሰራሽ ሐይቅን የሚያስተዳደር የአሣ ልማት ኮሚቴ መቋቋሙ ሃብቱን በአግባቡ ለማልማትና ለመጠቀም እንደሚያስችል የአማራ ክልል የእንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ አስታወቀ። የተከዜ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ከሚያዋስናቸው የአማራና የትግራይ ክልሎች አምስት ወረዳዎች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ኮሚቴው ወደ ሥራ መግባት በሚችልበት ሁኔታ ላይ በሰቆጣ ከተማ መክረዋል። በኤጀንሲው የአሳ ባለሙያ የሆኑት አቶ ቻላቸው አራጋው እንዳሉት የአሳ ልማቱን በበላይነት የመጠበቅና የማስተዳደር ተግባር የአካባቢው ማህበረሰብ ኃላፊነት ነው። በቀበሌ ደረጃ በሐይቁ የሚገኘውን የአሳና ሌሎች ሀብቶች የሚስተዳድር ኮሚቴ ከታች ጀምሮ በየደረጃው እንዲዋቀር መደረጉም ለእዚህ መልካም መሆኑን አመልክተዋል። አቶ ቻላቸው እንዳሉት የኮሚቴው መቋቋም በተበታተነ መልኩ ይካሄድ የነበረውን የአሳ ግብይት ስራአትን በማስቀረት ግብይቱ ዘመናዊና ሳይንሳዊ አሰራርን ተከትሎ ለአገር ጥቅም ለማዋል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። የነበረውን የገበያ ትስስር ችግር መቅረፍ በአሳ ማስገር የተደራጁ ማህበራትን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድገውም አመለክተዋል። ለእዚህም የጣና ሐይቅ የህብረተሰብ ተሳትፏዊ የአሳ አስተዳደር ተሞክሮን ወደ ተከዜ ሰው ሰራሽ ሐይቅ በማምጣት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ውጤት እየታየበት መሆኑን ነው የገለጹት። በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የእንስሳት ሃብት ልማት መምሪያ የአሳ ልማት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ዝናቡ ፍቃዱ እንዳሉት በሐይቁ ከ2 ሺህ 400 በላይ አስጋሪዎች በሽርክና ማህበር ተደራጅተው የአሳ ሀብቱ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ይሁን እንጅ በሐይቁ ወጥ በሆነ መልኩ የአሳ ልማት ስርአቱን የሚከታተል ኮሚቴ ባለመቋቋሙ  በዘርፉ ህገ ወጥ ንግድና የተከለከሉ መረቦችን መጠቀም በአሳ ሃበቱ ላይ ጉዳት ሲያደርስ እንደነበር አስታውሰዋል። “በአሁኑ ወቅት ከጸጥታ አካላት፣ ከአሳ አስጋሪ ማህበራት፣ ከአካባቢ ጥበቃና ከአካባቢው ማህበረሰብ የተወጣጣ ኮሚቴ መቋቋሙ የአሳ ልማቱን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው” ብለዋል። በውይይቱም ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ዞን የተዋቀረው ኮሚቴ ሥራውን እንዴትና በምን መልኩ  ተቀናጅቶ መስራት አንዳለበት የጋራ አቅጣጫ ተቀምጧል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከልም የሰሃላ ሰየምት ወረዳ ነዋሪ ወጣት ሃብቱ ዘገየ እንዳለው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ከጓደኞቹ ጋር በአሣ ማምረት ሥራ ተደራጅቶ እየሰራ ይገኛል። “የማህበራችን አባላት የምናመርተውን አሣ ባለሃብት ባወጣው ዋጋ እንጂ ተደራድረን እየሸጥን አይደለም” ያለው ወጣቱ በእዚህም በሰሩት ልክ ለውጥ ማምጣት እንዳልቻሉ ነው ያስረዳው። በሐይቁ የአሣ አስተዳደር ኮሚቴ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ መቋቋሙ ይህን ችግራችንን በመቅረፍ በተሰማራንበት ዘርፍ ጤታማ እንድንሆን ያስችለናል” ሲልም ገልጿል። በሰሜን ጎንደር ጠለምት ወረዳ በ2007 ዓ.ም በማህበር ተዳርጅቶ በአሳ ማስገር ሥራ ላይ የተሰማራው ሌላው ወጣት ታደሰ አዳነ በበኩሉ በሐይቁ ላይ የተከለከሉ መረቦችን የሚጠቀሙና ህገ-ወጥ አስጋሪዎች በመበራከታቸው በሥራቸው ላይ ችግር ሲፈጠር መቆየቱን ተናግሯል። “ያመረትነውን አሳ ባለሃብቱ ዋጋ ስለሚያሳጣብን ባለን አቅምና ሐይቁ ባለው የአሳ ክምችት ልክ ለማምረት እንዳንነሳሳ አድርጎን ቆይቷል” ብሏል። በአሁኑ ወቅት ተሳትፏዊ የአሳ አስተዳደር ኮሚቴ በቀበሌ ደረጃ መቋቋም መቻሉ ለአሳ ልማቱ ብሎም በማስገር ሥራ ለተሰማሩት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም አመልክቷል። በተከዜ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ከ3 ሺህ በላይ የአሳ አስጋሪዎች ያሉ ሲሆን በየዓመቱ እስከ 70 ሺህ ኩንታል የአሣ ምርት ለገበያ እየቀረበ ይገኛል። ለአምስት ቀናት በተካሄደው መድረክም የሰው ሰራሽ ሐይቁ ከሚያዋስናቸው ዝቋላ፣ ሰሃላ፣ አብርገሌ፣ ጠለምት እና ጠንቋ አበርገሌ ወረዳዎች የተውጣጡና የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም