የድሬዳዋ ገንደ ተስፋ ወጣቶች ያለባቸውን የሥራ አጥነት ችግር እንዲፈታላቸው ጠየቁ

70
ድሬዳዋ መስከረም 14/2011 የድሬዳዋ ገንደ ተስፋ ወጣቶች በአካባቢያቸው የሚስተዋሉ የመሠረተ ልማትና  የሥራ እጥነት ችግሮች  እንዲፈቱላቸው ጠየቁ ። የድሬዳዋ ገንደ ተስፋ ወጣቶች ከአስተዳደሩ አመራሮች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባካሄዱት ውይይት እንደተናገሩት ወጣቶቹ ለበርካታ ዓመታት በድሬዳዋ በተካሄደው ልማት እኩል እንዲሳተፉና እንዲጠቀሙ  አልተደረጉም፡፡ ወጣት ኢብሳ አህመድ እንደሚለው ይህ ሂደት ወጣቶችን ለከፋ የሥራ እጥነት ችግር የዳረጋቸው መሆኑንና ህይወታቸውን እንዳያሻሽሉ እንቅፋት ፈጥሮባቸዋል፡፡ ሌላው ወጣት ኤሊያስ መሐመድ በበኩሉ በአካባቢው የመንገድ፣ የጎርፍ መውረጃ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃና የኤሌክትሪክ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ባለመሟላቱ ህብረተሰቡንና ወጣቱ ለከፋ ማህበራዊ ችግሮች ተዳርገዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች በፍጥነት በመፍታት ወጣቱ የአካባቢው ልማት ግንባር ቀደም ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ወጣት ኤሊያስ አሳስቧል፡፡ የአካባቢውን ሰላምና ልማት በመጠበቅ ረገድ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወጣት አሊ ሙሳ ነው። እርሱን ጨምሮ ከ60 በላይ ወጣቶች በማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት በመታቀፍ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጾ፣ ሰሞኑን በሰዎች ቤት ቀለም በመቀባት ችግር ለመፍጠር የሞከሩትን አካላት ተደራጅተው ለመለየት እንደሚሰሩ ገልጿል፡፡ የወጣቱን ቀጣይ ህይወት ማስተካከል ለአካባቢውና ለድሬዳዋ ሰላምና ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አመልክቷል። አቶ ዮናስ ከበደ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጎን ለጎን ቤት ተከራይተው የሚኖሩ ፀጉረ ልውጦችን ማንነት መለየትና አከራዮችም ስለሚያከራዩዋቸው ሰዎች ትክክለኛ መረጃ ለፍትህ አካላት ማሳወቅ እንደሚገባቸው ገልፀዋል፡፡ ውይይቱን የመሩት የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር  ከድር ጁሃር "ወጣቶች ያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢና ትክክለኛ መሆናቸውን ተናግረው፣ አስተዳደሩ ወጣቶችን በማደራጀት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይሰራል" ብለዋል፡፡ ወጣቶቹ ለድሬዳዋ  ከተፈቀደው ተዘዋዋሪ ፈንድም ሆነ በአስተዳደሩ በሚኪያሄዱ የልማቶች ስራዎች ውስጥ ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል። የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሊድ መሐመድ በበኩላቸው የድሬዳዋ ነዋሪ  በተለይም ወጣቱ በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ መንፈስ ወደኋላ ለመመለስ የሚከናወኑ ተግባራትን ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት ገልጸዋል። ህዝቡ ከፍትህ አካላት ጋር ተቀናጅቶ አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን የጀመራቸውን ተግባራት ማጠናከር  እንዳለበት አሳስበው አስተዳደሩ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመራቸውን ሥራዎች ያጠናክራል፡፡ የሣቢያን ቀበሌ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ በሻህ ቀበሌው የገንደ ተስፋ እና የሌሎች አካባቢዎችን ወጣቶች የልማትና የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የመሆን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት የጀመረውን ሥራ እንደሚጠናከር አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም