በአማራ ክልል የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ መንጋ በአውሮፕላን በታገዘ የኬሚካል ርጭት ለመከላከል ዝግጅት እየተደረገ ነው

189

ባህርዳር፣ ጥቅምት 17/2015 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የተከሰተው የግሪሳ ወፍ መንጋ በደረሰ የመኽር ሰብል ላይ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ለመከላከል በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ተወካይ ዳይሬክተር አቶ አበበ አናጋው ለኢዜአ እንደገለጹት የግሪሳ ወፍ መንጋው  ከዚህ ወር መጀመሪያ ጀምሮ በሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች ተከስቷል።

መንጋው በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በከሚሴ ከተማና  በጂሌ ወረዳ እንዲሁም  በሰሜን ሸዋ ዞን ቀወትና ኤፍራታና ግድም ወረዳዎች መከሰቱን ተናግረዋል።

የአካባቢው አርሶ አደሮች  መንጋውን በባህላዊ መንገድ በወንጭፍና ድምፅ በማሰማት ለመከላከል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል ።

በአርሶ አደሩ ደረጃ በባህላዊ መንገድ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ከፌደራል ግብርና ሚኒስቴር ጋር በመሆን  መንጋውን ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ የመንጋው ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ  በደረሰ የመኽር ሰብል በተለይም በማሽላ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ  ርጭቱን ፈጥኖ ለማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል ።

በሸዋ ሮቢት የሚገኘውን የአውሮፕላን መንደርደሪያና ማረፊያ ሜዳን የማስተካከል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ለአብነት ጠቁመዋል።

ቢሮው ከየወረዳዎቹ የግብርና ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች ጋር በመሆን መንጋው የሚያድርባቸው ዘጠኝ ረግረጋማና ቁጥቋጧማ ቦታዎችን የመለየት ስራ መሰራቱን ጨምረው አመልክተዋል።

የመንጋው ማደሪያ በሆኑ በእያንዳንዱ ቁጥቋጧማና ረግረጋማ ቦታዎች ከ50 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን የሚደርስ የግሪሳ ወፍ ክምችት እንዳለ ተለይቶ መታወቁን ጠቁመዋል ።

የአውሮፕላን ማረፊያና መንደርደሪያ ጥርጊያ ቦታን የማስተካከል ስራው ተጠናቆ በቀጣይ ሳምንት የኬሚካል ርጭት ስራው እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

በአካባቢዎቹ ባለፈው ዓመት ተከስቶ የነበረን የግሪሳ ወፉ መንጋ  በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በባህላዊና ዘመናዊ መንገድ መከላከል እንደተቻለ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም