የወባ በሽታን ለመቆጣጠር የሚያግዝ 550 ማይክሮስኮፕ እና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ

175

ጥቅምት 17/2015 (ኢዜአ) የጤና ሚኒስቴር የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዝ የ550 ማይክሮስኮፕ እና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉ ከ550 ማይክሮስኮፕ በተጨማሪ ሌሎች የላቦራቶሪ መመርመሪያ ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

የተደረገው ድጋፍም አጠቃላይ 45 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በወቅቱ እንደተናገሩት የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ብሎም ለማስወገድ በሚደረገው ርብርብ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት የሚያደርጉት ድጋፍ ውጤታማ ነው፡፡

አሁን የተደረገው ድጋፍ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ በ6 ክልሎች በሚገኙ የጤና ተቋማት አገልግሎት ላይ እንደሚውሉ ገልፀዋል፡፡

ድጋፉን ያደረጉት የዩኤስ ኤይድ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ቲሞቲ ስቲን የወባ በሽታን በመዋጋት ረገድ ያለው አጋርነት ወደፊትም ይቀጥላል ብለዋል።

የሌላኛው ድጋፍ አድራጊ አይካፕ ዳይሬክተር ዶክተር ዘነበ መላኩ ለጤናው ዘርፍ የሚያገለግሉ 550 ማይክሮስኮፖች እና ሌሎች 50 የተለያዩ ለወባ መመርመሪያ ላብራቶሪ የሚሆኑ ግብዓቶችን በማቅረባችን ደስተኛ ነን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም