አየር መንገዱ አዲስ የኤርፖርት ከተማ ሊገነባ ነው---አቶ ተወልደ ገብረማርያም

120
አዲሰ አበባ መስከረም 14/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓመት 80 ሚሊዮን መንገደኞችን ሊያሰተናገድ የሚችል አዲስ የኤርፖርት ከተማ በቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በበጀት ዓመቱ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ  አቅራቢያ “አቡ ሴራ'' በምትባል ትንሽ መንደር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳደሪ የሆነ የኤርፖርት ከተማ ለመገንባት ዝግጅት ማጠናቀቁን ነው የገለጹት። በግንባታው ወቅትም በኤርፖርቱ አራት የማኮብኮቢያ ስፍራዎች፣ ትልልቅ ሆቴሎች፤ መንገደኞች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ከቀረጥ ነጻ የሆነ ግብይት የሚያካሄዱበት ስፍራና ትልቅ የካርጎ ሎጂስቲክ ማዕከል እንደሚኖረውም ገልጸዋል። በስፍራው የሎጂስቲክ ማዕከሉ መኖር በዱከምና ቦሌ ለሚ ለሚገኙ ኢንዱስትሪያል ፓርክች እንዲሁም አዳማ ላይ ለሚቋቋመው ኢዱስትሪያል ፓርክ ቅርብ በመሆኑ ትልቅ የኢዱስትሪያል ሎጂስቲክ ማዕከል እንደሚሆንም ተገልጿል። በሌላ በኩል በስፍራው እንደ አውሮፕላን ጥገና፣ አንዳንድ የአውሮፕላኖች አካል ማምረቻ፣ የአቪየሽን ኮንሰልታንሲና ዘርፈ ብዙ ስራዎች የሚከናወኑበት ስፍራ እንደሚኖረውም  አክለዋል። በከተማዋ አቅራቢያ የሚገኙ አርሶ አደሮችም የምግብ ግብዓት በማቅረብ የገበያ ትስስር የሚፈጥርላቸው  ሲሆን የሰው ኃይልንም ከመቅጠር አኳያ ለብዙ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥርላቸው ተገልጿል። በአዲስ አበባ ዙሪያ ሰባት ቦታዎችን ለኤርፖርቱ መገንቢያ የተመለከቱ ሲሆን በቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው  “አቡ ሴራ'' የተባለው ስፍራ ለፕሮጀክቱ ተመራጭ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው። ስፍራውም ሊመረጥ የቻለበት ምክንያት ዛሬ ያለንበት የአዲስ አበባ አየር ማረፊያ ከባህር ወለል በላይ 2ሺህ 400 ሜትር ሲሆን “አቡ ሴራ'' ግን ወደ 1ሺህ ዘጠኝ መቶ ሜትር ዝቅ ስለሚል እንደሆነም ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል። ይህ ሲሆን ደግሞ  የአውሮፕላኖችን የመነሳት ኃይላቸው ስለሚጨምር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሏል። ስፍራውን ተረክቦ ወደ ስራ ለመግባት ከኦሮሚያ ክልል መንግስትና ከአየር ኃይል ጋር በመነጋገር ወደ ስራ እንደሚገባ ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለዋል። አየር መንገዱ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ከዓለማችን ምርጥ 10 የአየር መንገዶች ተርታ ያሰልፈናልም ተብሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም