የወባ በሽታን ለመከላከል ለሕብረተሰቡ አጎበር የማሰራጨት ሥራ ተጀምሯል---የጤና ሚኒስቴር

199

ባህር ዳር ጥቅምት 16 ቀን 2015 (ኢዜአ) የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል 19 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአልጋ አጎበር ለሕብረተሰቡ ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አሰታወቀ ።

"ወባን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል" በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ ወባን የመከላከል ሳምንት በምዕራብ ጎጃም ዞን ባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ ዛሬ ተጀምሯል።

በንቅናቄው ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጀ ድጉማ እንደገለጹት፤ ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም ለማጥፋት ስትራቴጂ ተነድፎ በተሠራው ሥራ የወባ በሽታ ስርጭትን መቀነስ ተችሎ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የወባ በሽታ ስርጭት መልሶ እያገረሸ  የመምጣት አዝማሚያ ማሳየቱን ጠቁመው፤ ለዚህም አየር ንብረት ለውጥ እና የህብረተሰቡ መዘናጋት ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በ2014 ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በወባ ተይዘው ሕክምና ማግኘታቸውን ገልጸው ይህም በ2013 በበሽታው ተይዘው ሕክምና ካገኙት ጋር ሲነጻጸር የ10 በመቶ ብልጫ እንዳለው ዶክተር ደረጄ ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመትም 648 ሺህ በላይ ዜጎች በወባ በሽታ መያዛቸውን መረጃዎች እንደሚያሳዩ ጠቁመው፣ "ይህም በሽታው እያገረሸ መምጣቱን አንድ ማሳያ ነው" ብለዋል።

ወባን ለመከላከል 19 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአልጋ አጎበር ለህብረተሰቡ ለማዳረስ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን፣ "እስካሁንም 500 ሺህ የሚጠጋ የአልጋ አጎበር ወደሀገር ውስጥ ጎብቶ ለክልሎች የማከፋፈል ስራ ተሰርቷል" ብለዋል።

እስከ አንድ ወር ባለ ጊዜ ውስጥ በሁሉም ክልሎች 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን አጎበር እንደሚሰራጭ ጠቁመው፣  በቀጣይ ሁለት ወራት ቀሪውን አጎበር ወደ ሀገር በማስገባት የማከፋፈል ሥራ እንደሚሠራም አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በ2 ሚሊዮን ቤቶች ኬሚካል ለመርጨት መታቀዱን የገለጹት ዶክተር ደረጄ፣ ለእዚህም የኬሚካል ግዥ በመፈጸም ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ አንዳሳ ቀበሌ የአጎበር እደላው የተጀመረ ሲሆን፤ ህብረተሰቡ አጎበሩን ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲያውል አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱል ከሪም መንግስቱ በበኩላቸው፤ "የአማራ ክልል 80 በመቶ የሚሆነው አካባቢ ለወባ መራቢያ አመቺ ነው" ብለዋል።

ወቅቱም የወባ ትንኝ የምትራባበት በመሆኑ እንደ ክልል ንቅናቄ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አቶ አብዱልከሪም ገለጻ፤ የአጎበር ተደራሽ አለመሆን፣ የኬሜካል ርጭት እጥረት፣ የአየር ንብረት ለውጥና ህብረተሰቡ በእጁ ላይ ያሉ አጎበሮችን በአግባቡ መጠቀም አለመቻል የወባ በሽታ መልሶ እንዲያገረሽ አድርገኋል።

የወባ በሽታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችንም ስለሚያስከትል በየደረጃው ያለ አመራር ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራም አሳስበዋል።

የአንዳሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር የቻለ ባየ አዲሱ አጎበር በሽታውን ለመከላከል እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።

የአልጋ አጎበርን በአግባቡ መጠቀም የወባ በሽታን ለመከላከል ስላለው ጥቅም በቂ ግንዛቤ እንዳላቸው የገለጹት ሌለኛዋ የአጎበር ተጠቃሚ ወይዘሮ አንቺነሽ ቻሌ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም