የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዋንኛ ተልዕኮ አሸባሪው ሕወሓት ሰብአዊ ጋሻ ያደረጋቸውን ንጹሃን ዜጎች ነጻ ማውጣት ነው- የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ገጽ

290

ጥቅምት 15 2015 (ኢዜአ) “የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዋንኛ ተልዕኮ የሽብር ቡድኑን ወታደራዊ አቅም ማዳከምና ቡድኑ ሰብአዊ ጋሻ ያደረጋቸውን ንጹሃን ዜጎች ነጻ ማውጣት ነው” ሲል የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ገጽ አስታወቀ።

የሽብር ቡድኑ “ንጹሃን ዜጎች ጉዳት ደርሶባቸዋል” በሚል በርካታ ያቀናበራቸው ሐሰተኛ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማስረጃነት መገኘታቸውን አመልክቷል።

አሸባሪው ሕወሓት በጦር ሜዳ የገጠመውን ከፍተኛ ሽንፈት ለመሸፋፈን በቁጥጥሩ ስር ያሉ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም “ንጹሃን ዜጎች እየሞቱ ነው በሚል ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲፈጠር ሙከራ እያደረገ ነው” ሲል የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ገጽ በመግለጫው አስታውቋል።

የሽብር ቡድኑ “የንጹሃን ዜጎች ሞት” ሐሰተኛ ትርክት አላማ "ለአደጋ ተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም የሴቶችና ሕጻናት ጉዳትና ሞት ዓለም አቀፍ ቁጣና ውግዘት ያመጣልኛል” የሚል እንደሆነ አመልክቷል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዋንኛ ተልዕኮ የሽብር ቡድኑን ወታደራዊ አቅም ማዳከምና ቡድኑ ሰብአዊ ጋሻ ያደረጋቸውን ንጹሃን ዜጎች ነጻ ማውጣት እንደሆነ ገልጿል።

ሁሉም ተዋጊ አሐዶች በግጭት ቀጠናዎች የንጹሃን ዜጎችን ጥበቃን አስመልክቶ በቂ ስልጠና መውሰዳቸውንና በተለያዩ ቀደምት የግዳጅ አፈጻጸማቸው ስኬታ መሆኑን ማስመስከራቸውን አመልክቷል።

“አሸባሪው ሕወሓት ንጹሃን ዜጎችን አደጋ ላይ በመጣል ሐሰተኛ ተጎጂዎችን በመፈብረክ” በርካታ ያቀናበራቸው ሐሰተኛ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማስረጃነት መገኘታቸውን ገልጿል።

በሌላ በኩል “የአየር ድብድባ ተፈጽሟል በሚል ከሰሞኑ ሲሰራጩ የነበሩ ምስሎች አግኝቻለሁ” ያለው የማጣሪያ ገጹ ምስሎቹ ሐሰተኛና በተባሉት ቦታዎች ምንም አይነት እርምጃ አለመወሰዱን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም